የጤና መድኅን አገልግሎትን በስኬታማነት ማከናወን የመሪዎች ቁልፍ ተልዕኮ ነው።

2
ሁመራ: ታኅሣሥ 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የዞኑን ነዋሪዎች በሙሉ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲኾኑ እየሠራ መኾኑን በአማራ ክልል የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ጤና መምሪያ አስታውቋል።
የዞን እና የወረዳ መሪዎች የተሳተፉበት የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2018 በጀት ዓመት የንቅናቄ መድረክ በሁመራ ከተማ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የዞኑ ዋና አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው ጤናማ ማኅበረሰብ እንዲኖር የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን አገልግሎትን በስኬታማነት ማከናወን የመሪዎች ቁልፍ ትልዕኮ ነው” ብለዋል።
ማኅበረሰቡን የጤና መድኅን ተጠቃሚ ለማድረግ ከመሥራት ባሻገር ማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት መስጠት እንደሚያስፈልግም አቶ አሸተ ገልጸዋል። ለማኅበረሰቡ በቂ የኾነ የመድኃኒት አቅርቦት ለማድረስ በትኩረት ሊሠራበት እንደሚገባም አሳስበዋል።
ከሰሞኑ ለመሪዎች የተሰጠው ሥልጠና በተግባር ከሚፈተሽባቸው ተግባራት አንዱ የጤና መድኅን አገልግሎትን በአግባቡ መፈጸም መኾኑንም ጠቁመዋል።
የጤና መድህን አገልግሎት ውጤታማነት ለጤና ተቋማት ብቻ የሚተው አለመኾኑን የተናገሩት ደግሞ በብልጽግና ፓርቲ የዞኑ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ገብረእግዚአብሔር ደሴ ናቸው። አገልግሎቱን በጥራት እና በተደራሽነት ለማስፋት የሁሉም መሪዎች ድርሻ ነው ብለዋል።
ማኅበረሰቡ፣ አጋር አካላት እና የጤና ተቋማት ተቀናጅተው ተግባራትን በማከናወን የጤና መድኅን አገልግሎቱን በላቀ ሁኔታ መፈጸም ይገባል ብለዋል።
በ2018 በጀት ዓመት የነባር አባላትን ደብተር በማደስ እና አዳዲስ አባላትን ደግሞ በአግልግሎቱ በማቀፍ የዞኑን ማኅበረሰብ በሙሉ የጤና መድኅን አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ ነው ሲሉ የዞኑ ጤና መምሪያ ኀላፊ ስማቸው ግደይ ተናግረዋል።
በባለፈው 2017 በጀት ዓመት 76 በመቶ የዞኑ እማወራዎች እና አባወራዎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መኾናቸውን ያነሱት መምሪያ ኀላፊው በተያዘው በጀት ዓመት ደግሞ መቶ በመቶ ማኅበረሰቡ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲኾን በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።
ባለፉት ዓመታት የጤና መድኅን አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የመድኃኒት አቅርቦት እጥረት መኖሩን ያኑሰት አቶ ስማቸው ይሄንን ችግር ለመቅረፍ በአራቱ ወረዳዎች እና በአምስቱ ከተማ አሥተዳደሮች የማኅበረሰብ አቀፍ መድኃኒት ቤት ለመክፈት እየተሠራ መኾኑንም አስረድተዋል።
በ2017/18 በጀት ዓመት ኅብረተሰቡን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት ውጤት የታየባቸው ናቸው ሲሉ ተሳታፊዎች ለአሚኮ ተናግረዋል።
በተያዘው ዓመትም ነባር አባላትን ጨምሮ አዳዲስ አባላትን በሙሉ አቅም በማሳተፍ የንቅናቄ መድረኩ መነሳሳት እንደፈጠረላቸው ነው የተናገሩት።
መድረኩ ከሰሞኑ ሲሰጥ ከነበረው የመሪዎች ሥልጠና ማግስት መከናወኑ ለጤና መድኅን አገልግሎቱ ውጤታማነት የበኩሉን ድርሻ እንዳለው ተሳታፊዎቹ ጠቅሰዋል።
ዘጋቢ፦ አምሳሉ አሞኘ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየዲስክ መንሸራተት ምንደድን ነው?
Next articleጤናማ እና አምራች ኃይል ለማፍራት ማኅበረሰቡን የጤና መድኅን ተጠቃሚ ማድረግ ይገባል።