የዲስክ መንሸራተት ምንደድን ነው?

21
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በሽታው አስቸጋሪ ስሜት ያለው ለመንቀሳቀስ፣ ለመቀመጥ፣ ጎንበስ ብሎ የፈለገውን እቃ ለማንሳት የሚቸግር ትልቅ እክል የሚፈጥር ነው።
ወይዘሮ አዝመራ ጌጤ የዚህ በሽታ ተጠቂ ናቸው። ወይዘሮዋ በመጀመሪያ በሽታው ሲጀምራቸው ያለምንም ጉዳት ወገቤን አመመኝ እያልኩ ለሰዎች ማውራት ጀመርኩ አሉን። ሕመሙ እየተባባሰ መጣና መኝታም አለመመቸት፣ ለመቀመጥ መቸገራቸውን ነገሩን።
ወደ ጤና ተቋም በመሄድ የአልትራሳውንድ እና ኤም አር አይ ምርመራ ማድረጋቸውን ያስታውሳሉ። ከምርመራው በኋላ የዲስክ መብለዝ እና ትንሽ መንሸራተት ያመላክታል ተብለዋል።
ሕመሙን ለማስታገስ የማስታገሻ መድኃኒት ከመውሰድ በተጨማሪ ቀለል ያለ የፊዚዮቴራፒ አገልግሎት ጀመርኩ ይላሉ።
ወይዘሮ አዝመራ ስለሕመሙ ስሜቱን ሲናገሩ እጂግ አስቃቂ፣ ለስቃይ የሚዳርግ እና እንደፈለኩ ጎንበስ ቀና ብሎ ለመንቀሳቀስ ጭንቅ የሚፈጥር ነው ብለውታል።
አሁን የተሻለ ደኅንነት እየተሰማቸው እንደኾነ የጠቀሱት ወይዘሮዋ ነገር ግን ከበድ ያሉ ሥራዎችን ሲሠሩ ሕመሙ እንደሚሰማቸው ገልጸዋል።
ሕመሙ እንክብካቤ የሚወድ እና በሕክምና ባለሙያዎች የሚሰጥን ምክር በጥንቃቄ መተግበር እንደሚጠይቅም አንስተዋል።
✍️ ለመኾኑ ዲስክ ምንድን ነው? ምልክቶቹ እና ሕክምናውስ? እንዴትስ ይታከማል?
ዶክተር ምንተስኖት ፍጥረቱ በአዲስ አበባ ተክለ ሃይማኖት ጠቅላላ ሆስፒታል ጠቅላላ ሐኪም ናቸው።
ዲስክ ፕላስቲክ የመሰለ ተለጣጭ ወይም ለስለስ ያለ በጀርባችን ባሉ አጥንቶች መካከል የሚገኝ እና አጥንቶቹ እርስ በእርሳቸው እንዳይፋተጉ እና ለነርቭ ጉዞ እንዲመች የሚያደርግ የጀርባ አጥንት ክፍል ነው አሉን።
ዲስክ በተለያየ ሁኔታ ሊጎዳ የሚችል ሲኾን በጉዳት ምክንያት ያለበትን ቦታ በመሳት ወደ ጎን አልያም ወደ ጀርባ አጥንት በመጠጋት የነርቭ ሕዋሳትን ይጫናል አሉን።
ይህ ነርቭ ላይ በመጫን የሚከሰተው አልያም የሚፈጥረው ሕመም ወይም አጠቃላይ ሁኔታዎች የዲስክ መንሸራተት ይባላል።
ነርቭ የተለያዩ የሰውነት ክፍሎችን የሚያንቀሳቅስ ሲኾን በዲስክ መንሸራተት ወቅት በብዛት ወደ እግራችን የሚሄደው ነርቭ ላይ ጫና ስለሚፈጠር እግራችን አካባቢ ሕመም ሊሰማ ይችላል ይላሉ።
እንደ ዶክተር ምንተስኖት ገለጻ የዲስክ መንሸራተት ምልክቶች እግር ላይ የማቃጠል፣ የመዛል፣ የእግር ስሜት ማጣት፣ በምንቀመጥበት ጊዜ ከፍተኛ የኾነ የወገብ ሕመም መሰማት እና አንዳንዴ ለመተኛትም መቸገር ዋነኞቹ ናቸው።
በእንቅስቃሴ እና ተያያዥ ሁኔታዎች ከፍተኛ የወገብ እንቅስቃሴን የሚጠይቁ እና ከባድ እቃዎችን የሰውነታችንን ሚዛን ሳንጠብቅ እና ሳንዘጋጅ በምናነሳበት ወቅት ለዲስክ መንሸራተት ወይም መዛባት ሊዳርግ እንደሚችልም ሐኪሙ ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም የእድሜ መጨመር እና ተፈጥሯዊ ችግር ለዲስክ መንሸራተት ሕመም ሊያጋልጡ ይችላሉ።
በመጀመሪያ ደረጃ የሕመሙ ተጠቂ በሚሰማው የሕመም ምልክቶች ላይ የተመሠረተ ምርመራ ማድረግ ይኖርበታል። ኤም አር አይ በተሰኘ የሕክምና መሳሪያ በመታገዝ የነርቮችን እንቅስቃሴ የሚያሳይ ምርመራ ማከናወን እንደሚመከር ዶክተር ምንተስኖት ገልጸዋል።
የዲስክ መንሸራተት መኾኑ ከተረጋገጠ እና ዲስኩ በጣም ያልተጎዳ ከኾነ በቤት ውስጥ ታካሚው ቀላል እንቅስቃሴ እንዲያደርግ፣ ዋና እንዲዋኝ፣ ስፖርት እንዲሠራ የሚታዘዝ ሲኾን የሕመም ማስታገሻም ሊታዘዝም ይችላል ብለዋል።
ሕመሙ ለውጥ ሳያመጣ ከቀረ እና ከቀጠለ ማስታገሻ በመርፌ ይሰጣልም ብለዋል።
ከዚህ በላይ ሕመሙ ከተባባሰ በቀዶ ጥገና የተጎዳውን አካል በማስተካከል ሕመሙን ማስታገስ እንደሚቻል ዶክተር ምንተስኖት ነግረውናል።
ዘጋቢ:- ሰመሀል ፍስሀ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየመሪዎችን አቅም ወደ ተቋም ግንባታ ማሳደግ የትኩረት አቅጣጫ ነው።
Next articleየጤና መድኅን አገልግሎትን በስኬታማነት ማከናወን የመሪዎች ቁልፍ ተልዕኮ ነው።