
እንጅባራ: ታኅሣሥ 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር እንጅባራ ከተማ “በመደመር መንግሥት እይታ የዘርፎች እምርታ” በሚል መሪ መልዕክት ለዘጠኝ ቀናት በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሲሰጥ የቆየው የመካከለኛ መሪዎች ሥልጠና ተጠናቅቋል።
ሥልጠናው ሀገራዊ እና ክልላዊ ሁኔታዎችን በውል ተረድተው ወቅቱ የሚጠይቀውን መሪነት ለመስጠት የሚያስችል አቅም እንደፈጠረላቸውም ሠልጣኞች ተናግረዋል።
ከሥልጠናው ያገኙትን እውቀት እና ግንዛቤ ወደ ተግባር በመቀየር የሚመሩትን ሕዝብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ተግተው እንደሚሠሩም መሪዎቹ ገልጸዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አለሙ ሰውነት ሥልጠናው በመሪዎች መካከል የአስተሳሰብ እና የተግባር አንድነት በመፍጠር የዘርፎችን እምርታ ከግብ ለማድረስ የጠራ አቋም የተያዘበት መኾኑን ተናግረዋል።
የመደመር መንግሥት ህልሞችን እውን ለማድረግ “የመሪዎችን አቅም ወደ ተቋም ግንባታ ማሳደግ”እና ቀጣይነትን ማረጋገጥ በቀጣይ በትኩረት ይፈጸማልም ነው ያሉት።
የሥልጠና ጭብጦችን ሳይንጠባጠቡ ወደ መሬት በማውረድ ከዘርፎቹ እምርታ የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ከሠልጣኝ መሪዎች ተጠባቂ ተግባር መኾኑን ያስገነዘቡት ደግሞ የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ዋና አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው ናቸው።
የአካባቢ ጸጋዎችን በውል መረዳት፣ ጸጋዎችን ወደ ሃብት ለመቀየር የጠራ ዕቅድ ማቀድ እና በየጊዜው እየገመገሙ መምራት የመሪዎች የዘወትር ተግባር ሊኾን ይገባልም ነው ያሉት።
በሥልጠናው ማጠቃለያም ከሠልጣኞች የተሰበሰበ ለሰው ተኮር ተግባራት የሚውል 102 ሺህ ብር ለእንጅባራ ከተማ አሥተዳደር ተበርክቷል።
ዘጋቢ፦ ሳሙኤል አማረ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
