የበጋ መስኖ እርሻ የደቡብ ወሎ ዞን አርሶ አደሮችን ሕይወት እና ኑሮ እየቀየረ ነው።

8
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ በደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ወረዳ የበጋ ስንዴ እርሻ ሥራ አስጀምሯል። ሥራው የተጀመረው በጎለልሻ መስኖ ልማት ላይ ሲኾን የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን፣ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ ቃልኪዳን ሽፈራው እና ሌሎችም መሪዎች ተገኝተዋል። የቃሉ ወረዳ አርሶ አደሮችም ከመሪዎቻቸው ጋር በመኾን ሥራውን በንቅናቄ ጀምረዋል።
በሥራ ላይ ያገኘናቸው አርሶ አደር መሐመድ አብዱ እንዳሉት ከዚህ በፊት የክረምት ዝናብ ብቻ ጠብቀው ማሽላ ያለሙ ነበር። ይህም ኑሯቸውን እምብዛም የቀየረ እንዳልነበር አጫውተውናል።
የበጋ ስንዴ ልማት እሳቤ ከመጣ ወዲህ ግን ማሳቸው አልቦዘነም። ክረምት ማሽላ ይዘሩታል፤ በጋ ላይ በስንዴ ይሸፍኑታል፣ ጎን ለጎንም አትክልትና ፍራፍሬ ያለማሉ። ከአትክልትና ፍራፍሬ ብቻ በዓመት 200 ሺህ ብር ገቢ እንዳገኙ ነግረውናል።
“የእርሻ በሬ ለመግዛት እንኳን እቸገር ነበር፤ መስኖ ማልማት ከጀመርን ወዲህ ግን አምስት በሬዎችን ገዝቻለሁ፤ ተደራጅተን ትራክተር ለመግዛትም መንገድ ላይ ነን” ብለዋል አርሶ አደሩ።
የደቡብ ወሎ ዞን አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን እንዳሉት የ2018 ዓ.ም የበጋ ስንዴ ልዩ ትኩረት የተሰጠው የልማት ሥራ ነው። በዞኑ 41 ሺህ ሄክታር መሬት በበጋ መሥኖ ስንዴ እንደሚሸፈንም ገልጸዋል።
አርሶ አደሮች ከስንዴ በተጨማሪ ሌሎች አትክልትና ፍራፍሬዎችን እያለሙ ኑሯቸውን እየቀየሩ ስለመኾኑም አንስተዋል። አትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን ከራስ አትርፎ ለውጭ ገበያ ለማቅረብም ታልሞ እየተሠራ ነው ብለዋል።
እንደዞን ውስን የትራክተር ቁጥር መኖሩን የገለጹት አሥተዳዳሪው የትራክተሮችን ቁጥር በመጨመር ዘመናዊ እና ውጤታማ የእርሻ ሥራ ለማከናወን እየተሠራ ነው ብለዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ ቃልኪዳን ሽፈራው የዚህ ዓመት የበጋ መስኖ ልማት ከምንጊዜውም በላይ በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል። የስንዴ ዘር ሥራው ቀደም ብሎ በንቅናቄ ተጀምሯል፤ እስከ ታኅሣሥ ወር መጨረሻም ይጠናቀቃል ነው ያሉት።
እንደ ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር ያሉ አስፈላጊ የኾኑ ግብዓቶችን ለአርሶ አደሮች በወቅቱ ለማቅረብም ግብርና ቢሮው በቅንጅት እየሠራ ነው ብለዋል። የእርሻ ሥራው በቴክኖሎጅ ተደግፎ ለላቀ ውጤት እንዲበቃም ትራክቸሮች እየቀረቡ ስለመኾኑ ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየሰብዓዊ መብት አያያዝ እና የማኅበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ዘዴን የተመለከተ ሥልጠና በደብረ ብርሃን ከተማ እየተሰጠ ነው።
Next article“ከዚህ በላይ የግፍ ጽዋ እንዲፈስ መፍቀድ አይገባም” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)