
ደብረ ብርሃን: ታኅሣሥ 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ በሰብዓዊ መብት አያያዝ እና በማኅበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ዘዴዎች ዙሪያ በደብረ ብርሃን ከተማ ሥልጠና እየሰጠ ነው፡፡
የአማራ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የማኅበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ሥርጸት እና ተሞክሮ ቅመራ መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር ጋሻዬ መልካሙ ሥልጠናው የሰብዓዊ መብት አያያዝ ግንዛቤን ማሳደግ አላማው ያደረገ ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም የማኅበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ተግባርን ማሳለጥ የሚያስችሉ ክህሎቶችን ማስጨበጥ ሌላው ከዚህ ሥልጠና የሚጠበቅ ግብ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
“የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ሰላምን ከማስፈን ሥራችን ጎን ለጎን የምናከናውነው ተግባር ነው” ብለዋል ኮማንደር ጋሻዬ፡፡
ተጠርጣሪዎችን እና ጥፋተኝነታቸው የተረጋገጡ ወገኖች በፖሊስ ጣቢያዎች እና በማረሚያ ቤቶች ሰብዓዊ መብታቸው ተጠብቆ እንዲገለገሉ በማድረግ ሂደት በሥልጠናው የተሻለ አቅም እንደሚፈጥሩ ተሳታፊዎቹ ተናግረዋል፡፡
ቅጣት የተወሰነባቸው ግለሰቦች በእርምት ጊዜያቸውም ይሁን ኋላም ላይ ወደ ማኅበረሰቡ ሲቀላቀሉ የታረሙ እና የታነጹ ወገኖችን ለመፍጠር ሥልጠናው እገዛ እንደሚያደርግላቸው ተሳታፊዎቹ ገልጸዋል፡፡
ቢሮው ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት መርሐ ግብር ላይ በሰላም ዙሪያ ከሚሠራ ፕሮጀክት ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ ነው ሥልጠናውን እየሰጠ የሚገኘው፡፡
ዘጋቢ:- ገንዘብ ታደሰ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
