የአብቁተ ባንክ የመሆን ጥያቄ በሚቀጥሉት ሦስት ወራት ፈቃድ ያገኛል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስታወቁ፡፡

763

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 17/2012 ዓ.ም (አብመድ) አማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም (አብቁተ) አቀራረቡን የንግድ፣ ማዕከሉን ደግሞ ሕዝብ አድርጎ ወደ ባንክነት እንደሚሸጋገር ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ መኮንን የለውም ወሰን ተናግረዋል፡፡

ከሦስት አስርት ዓመታት በፊት በቁጥር ብልጫ ያለውን እና በዝቅተኛ ደረጃ የሚኖረውን የኅብረተሰብ ክፍል በምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴዎች የሚደግፍ የገንዘብ ተቋም አልነበረም፡፡ አሁን ላይ የሚደርሱት የማይክሮ (የአነስተኛ) ኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ተቋማትም ምስረታቸው ቢበዛ ከ25 ዓመታት አይበልጥም፡፡

በወቅቱ ሦስት ብቻ የነበሩት ንግድ ባንክ፣ ልማት ባንክ እና የቢዝነስ እና ኮንስትራክሽን ባንክ የማክሮ (ዐብይ) ኢኮኖሚው አንቀሳቃሽ የገንዘብ ተቋማት ናቸው፡፡ የከተሜነት ባህሪያቸው፣ ብድር ሲሰጡ ከብድሩ በላይ እስከ 150 በመቶ መያዥያ መጠየቃቸው እና የተጠና የንግድ እና የአዋጭነት ንድፍ መፈለጋቸው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚኖረው ሕዝብ አገልግሎት ሰጭ አልነበሩም፡፡

ይህን መሠረት አድርጎም በወቅቱ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኘው የኅብረተሰብ ክፍል የገንዘብ ምንጭ ሆኖ የሚያገለግል ተቋም ለማቋቋም የአስፈላጊነት ጥናት ተደረገ፡፡ ማኅበረሰቡ የሚጠቀምባቸው ሦስት ነባር የገንዘብ ምንጮች እንዳሉትም አብሮ ተመላከተ፡፡ የእምነት ተቋማትና ትንንሽ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ቤተሰብ እና አራጣ አበዳሪዎች የማኅበረሰቡ ነባር የገንዘብ ምንጮች መሆናቸው ተለየ፡፡ ይህንን መሠረት አድርጎ ነበር የአማራ ብድር እና ተቋም (አበቁተ) በሃገር ደረጃ የመጀመሪያው የማይክሮ ፋይናንስ ተቋም ሆኖ የተመሠረተው ብለዋል የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መኮንን የለውምወሰን፡፡ እንደ ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገለፃ አበቁተ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላለው ማኅበረሰብ የገንዘብ ምንጭ ሆኖ ሲቋቋም ሁለት ዓበይት ዓላማዎች ነበሩት፡፡ በተበጣጠሰ መንገድ የሚሰጠውን እና የሕዝቡን ኑሮ ያላሻሻለውን የአራጣ አበዳሪ ስሪት በማፍረስ የሕዝቡን የመልማት ፍላጎት የሚደግፍ ተቋም መሆን እና የማኅበረሰቡን የቁጠባ ባህል በእውቀት ላይ ተመስርቶ መደገፍ የሚሉ ነበሩ፡፡

የጥናቱን ግኝት መሠረት አድርጎ የተቋቋመው አበቁተ ወደ መደበኛ አገልግሎት ከመግባቱ በፊት በወቅቱ በክልሉ ከነበሩት 10 ዞኖች ውስጥ 29 ወረዳዎችን በመምረጥ በሙከራ ትግበራ ሥራ ጀመረ፡፡ ዛሬ ላይ ደግሞ በክልሉ ሁሉም ወረዳዎች ላይ ተደራሽ ከመሆን አልፎ በአብዛኞቹ ወረዳዎች ሁለት እና ሦስት ቅርንጫፎችን በመክፈት አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን አቶ መኮንን አስረድተዋል፡፡ በእያንዳንዱ የገጠር ቀበሌዎች 97 በመቶ ተደራሽ መሆኑንና 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቆጣቢ፣ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ተበዳሪ እና ጡረታን ጨምሮ 150 ሺህ የልዩ ልዩ አገልግሎቶች ተከፋይ ደንበኞች እንዳሉትም ገልጸዋል፡፡ አብቁተ ወደ ባንክ ለመሸጋገር በ2009 ዓ.ም የወጣውን አነስተኛ የገንዘብ ተቋማት ወደ ዐብይ የገንዘብ ተቋምነት መሸጋገርን በሚፈቅደው አዋጅ መሠረት ቀድሞ ጥያቄ ቢያቀርብም በተለያዩ ምክንያቶች መዘግየቱን ዋና ሥራ አስፈፃሚው ተናግረዋል፡፡ ዝርዝር የአፈፃፀም መመሪያው ፀድቆ እንደወጣም አበቁተ ሰነዶቹን አስገብቶ ወደ ባንክ የማደግ ፈቃድ ያገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ነው ያስረዱት፡፡

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ጌታቸው ይርጋ (ዶክተር) በባሕር ዳር ከተማ የሚገኙትን አብቁተን ጨምሮ በሁሉም ባንኮች የሚሰጡትን አገልግሎቶች በሚመለከት መረጃ ሰብስበው እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ሁሉም የገንዘብ ተቋማት በዝቅተኛ እና መካከለኛ ደረጃ ለሚገኙት የንግድ እና ጥቃቅን አገልግሎቶች የአሠራር ቦታ እንደሌላቸው ማረጋገጣቸውንም ጠቅሰዋል፡፡ ይህም የሚያመላክተው በክልሉ ላሉ አነስተኛ የንግድ አንቀሳቃሾች በቂ አገልግሎት የሚሰጡ የገንዘብ ተቋማት አለመኖራቸውን ነው ብለዋል፡፡ አገልግሎት ሰጪ አነስተኛ የገንዘብ ተቋማት እጥረት ባለበት የክልሉ ነባራዊ ሁኔታ አብቁተ ራሱን ወደ ባንክ ቢያሸጋግር የአነስተኛ ገንዘብ ተቋማት እጥረቱን እንደሚያባብሰውም ጠቅሰዋል፡፡ አበቁተ አሁን የያዛቸውን ደንበኞቹን “ይዥ እሸጋገራለሁ” ቢል እንኳን የባንክ አሠራር ስርዓቱ ስለማይፈቅድ እነዚህን ደንበኞች ጥሎ እንደመሸጋገር ይቆጠራልም ነው ያሉት፡፡

ዋና ሥራ አስፈፃሚው በበኩላቸው “አበቁተ አቀራረቡን የንግድ፣ ማዕከሉን ደግሞ ሕዝብ አድርጎ ወደ ባንክነት ይሸጋገራል” ብለዋል፡፡ ተቋሙ ወደ ባንክ ሲሸጋገር ደንበኞቹን እንደያዘ የሚያስቀጥል የአሠራር ስርዓት እንደሚዘረጋም አቶ መኮንን አስረድተዋል፡፡ “በአንድ ተቋም ጥላ ስር ሁለት አበይት ክንፎች ያሉት አሠራር ይዘረጋል፡፡ በመጀመሪያው ክንፍ የቀደሞ የነበሩትን ደንበኞቹን ይዞ አገልግሎቱን ያሰፋል፡፡ በሁለተኛው ክንፍ ደግሞ ታላላቅ የንግድ አንቀሳቃሽ ደንበኞችን እና የውጭ ንግድ ስርዓትን በሚያግዝ መልኩ ይደራጃል” ሲሉም በምጣኔ ሀብት ምሁሩ ለቀረቡ ስጋቶች የመፍትሔ አማራጮችን አስረድተዋል፡፡

በዚህ የዋና ሥራ አስፈፃሚው ማብራሪያ ላይ የምጣኔ ሀብት ሳይንሱ ቅራኔ ባይኖረውም እንኳን የፋይናንስ ህጉ ያሠራል ወይ የሚለው ጥያቄ ከንግድ ህግ አንፃር የሚታይ እንደሆነ ዶክተር ጌታቸው አስረድተዋል፡፡ አበቁተ የሕዝብ ሀብት በመሆኑ እና ሕዝቡ ደግሞ በተለያየ የምጣኔ ሀብት ደረጃ ስለሚገኝ የአሠራር ችግር ላለመፈጠሩ ራሱ አበቁተ እና የክልሉ መንግስት ሊያጤኑት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ በባንክ አሠራር ውስጥ ዋናው ቁምነገር ተወዳዳሪ ሆኖ መገኘት መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር ጌታቸው ይህም ሊታሰብበት የሚገባ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚው በበኩላቸው አብቁተ በዘርፉ ሂደታዊ በሆነ መንገድ ያካበተው በቂ ልምድ ያለው፣ የዘርፉን ሙያዊ የአሠራር እርሾ ያካበተ፣ በቂ የፋይናንስ አቅም እና የቴክኖሎጂ ሽግግርም እየገነባ ያለ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በ300 ሚሊዮን ብር እያበለፀገው ያለው የኮር ባንኪግና መረጃ ማዕከል እና በአዲስ አበባ በ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር እያስገነባቸው ያሉት ባለ 32 ፎቅ መንትያ ህንፃዎች ተጨማሪ ጉልበት እንደሚሆኑትም ነው አቶ መኮንን የተናገሩት፡፡ ላለፉት አራት ዓመታት ባንክ የመሆን ጥያቄ ሲያቀርብ የነበረው አብቁተ በሚቀጥሉት ሦስት ወራት ፈቃድ ያገኛል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስታውቀዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

Previous article“በዓባይ ጉዳይ የግብጽ አቋም ስህተትና ስግብግብነት የተሞላበት ነው፡፡” ኡስታዝ አቡበከር አህመድ
Next articleበኢትዮጵያ በላፉት 24 ሰዓታት ተጨማሪ 186 ሰዎች የኮሮናቫይረስ ተገኝቶባቸዋል፤ የሦስት ሰዎች ሕይወትም አልፏል፤ 74 ሰዎች ደግሞ አገግመዋል፡፡