
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከታኅሣሥ 3 እስከ ታኅሣሥ 6/2018 ዓ.ም ድረስ የሚካሄደውን የልጅነት ልምሻ (ፖልዮ) መከላከያ ክትባት በባሕር ዳር መቅረዝ አጸደ ሕጻናት ትምህርት ቤት አስጀምሯል።
በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩም ላይ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች እና አጋር አካላት ተገኝተዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ ኀላፊ ዓለም አሰፋ ፖሊዮ እጅ እና እግርን ሽባ የሚያደርግ እና አለፍ ሲልም የሚገድል በሽታ መኾኑን ገልጸዋል።
ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል በዘመቻው እንዲሳተፍ እና ባለድርሻ አካላት እንዲሁም መንግሥት እና ኅብረተሰቡ በባለቤትነት ሊሠሩት እንደሚገባ በመረሐ ግብሩ ላይ አስገንዝበዋል።
ሕጻናት በብዛት የሚገኙባቸው ተቋማት እንዲሁም የሕጻናት ቤተሰቦች ልጆቻቸውን በማስከተብ ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ በዘንድሮው የፖሊዮ ክትባት መርሐ ግብር እንደ ክልል ከ5 ሚሊዮን በላይ ሕጻናት ክትባቱን ያገኛሉ ብለዋል።
ዘጋቢ:- ሰመሀል ፍስሐ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
