የግብርና ሜካናይዜሽንን ለማስፋፋት የክልሉ ግብርና ቢሮ በትኩረት እየሠራ ነው።

10
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የግብርና ሥራን ማዘመን ዘርፉ ለኢኮኖሚ የሚኖረውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ ሚናው የጎላ ነው፡፡
የአርሶ አደሮችን ድካም፣ጊዜ እና የምርት ብክነትን በመቀነስ ተገቢውን ጥቅም ማግኘት የሚቻለው የግብርና ቴክኖሎጂን በአግባቡ መጠቀም ሲቻል መኾኑም ብዙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
የግብርና ሥራ የዜጎችን የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባለፈ ለሀገራዊ እድገትም የሚኖረውን ሚና ለማሳደግ ዘርፉን ማዘመን እና በትኩረት መደገፍ ይገባል፡፡
አርሶ አደር ሽመልስ ለታ በሰሜን ሸዋ ዞን ሲያ ደብርና ዋዩ ወረዳ የወለይ ደነባ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ አርሶ አደሩ ከ30 ዓመታት በላይ የግብርና ሥራ በመሥራት እንደሚተዳደሩ ተናግረዋል፡፡
ቀደም ባሉት ዓመታት እንደ ጥንት አባቶቻችን በበሬ አርሼ፣ በእጄ ኮትኩቼ እና አጭጄ ነበር ምርት የምሰበስበው ይላሉ አርሶ አደሩ፡፡
በዚህም ምርቱም ብዙ ውጤት አልነበረውም፤ በስብሰባ ወቅትም የሚባክነው እህል ቀላል የሚባል አልነበረም ብለውናል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዘመናዊ ማረሻን (ትራክተርን) በመጠቀም በ7 ሄክታር መሬት ላይ ጤፍ እና ስንዴን በዋናነት እንደሚያመርቱ የተናገሩት አርሶ አደሩ ምርትን በኮምባይነር በመሰብስብ እና በማጨድ ያለብክነት ወደ ጎተራዬ አስገባለሁ ብለዋል፡፡
ይኽም ውጤታማ አድርጎኛል፤ በአካባቢዬም ሞዴል አርሶ አደር ኾኛለሁ፤ ኑሮየንም አሻሽየ ጥሪት እንዳፈራ አስችሎኛል ነው ያሉት፡፡
የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ጥበቃ ቡድን መሪ አበበ ጌታቸው በዞኑ በ2017/2018 የምርት ዘመን ከ556 ሺህ በላይ ሄክታር በዘር ለመሸፈን ታስቦ ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል፡፡
ከዚህም 20 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይሰበሰባል ተብሎ ነው የሚጠበቀው፡፡ አሁን ባለው የሰብል ቁመና 18 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል ማግኘት እንደሚቻል የአንደኛ ዙር ሰብል ግምገማ መረጃ ያሳያል ነው ያሉት፡፡
ወቅቱ የሰብል መሰብሰቢያ ወቅት እንደመኾኑ መጠን እስካሁን ባለው ከ409 ሺህ ሄክታር በላይ ሰብል ማሰባሰብ ተችሏል ነው ያሉት፡፡
ከዚህ ውስጥ 217 ሺህ ሄክታር የሚኾነውን በመውቃት ከ6 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ማግኘት ተችሏል ብለዋል፡፡
ዞኑ በሜካናይዜሽን መሰብሰብን ትልቅ ትኩረት በመስጠት እያሠራ ያለ ዞን ነው ያሉት ቡድን መሪው ከተሰበሰበው ምርት ውስጥ ከ1 ሺህ 394 ሄክታር በላይ የሚኾነው በኮምባይነር የመውቃቱን ተናግረዋል፡፡
ኾኖም በኮምባይነር ምርትን የመሰብሰብ ሥራው በቂ ነው ብሎ መውሰድ አይቻልም ነው ያሉት፡፡
ለዚህም ሰፋፊ ክላስተር ያሉባቸው አካባቢዎችን እንደነ ሲያደብር፣ ሞጃና ወደራ፣ ሞረትና ጁሩ፣ አንጎለላና ጠራ እና ባሶና ወረና በሚባሉ ወረዳዎች በቀጣይ ለሚደርሱ ሰብሎች በስፋት ዘመናዊ መሳሪያን በመጠቀም የማሰባሰብ ሥራ እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡
በአጠቃላይ ዞኑ ከ91 በላይ የሚኾኑ የቴክኖሎጂ ግብዓቶችን ተጠቅሞ የድህረ ምርት ብክነት እንዳይፈጠር ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መኾኑን ነው ያብራሩት፡፡
ሰብሉ ከተሰበሰበ በኋላም በጎተራ ውስጥ በተባይ አማካኝነት የሚከሰት ብክነትን ለመቀነስ ፒክስ ባግ ቴክኖሎጂን በመጠቀም እንዲከዝኑ ለአርሶ አደሮች የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ በመሥራት ግብዓቱ ተደራሽ እንዲኾን ማድረግ ተችሏልም ብለዋል፡፡
የግብርና የገጠር ሽግግር እውን እንዲኾን የግብርና ሜካናይዜሽን መጠቀም ይገባል ያሉት የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ ደረጀ ማንደፍሮ ናቸው፡፡
ለዘመናት በበሬ ትክሻ ሲያርሱ፣ በሰው ጉልበት ምርት ሲሰበስቡ፣ በእንስሳት ጉልበት ምርትን ከገለባ ሲለዩ የነበሩ አርሶ አደሮች ጊዜ እና ጉልበት ቆጣቢ፣ ምርቱ ሳይባክን የሚሰበስብበት የግብርና ሜካናይዜሽን መጠቀም ይኖርበታል ብለዋል፡፡
በክልሉ የግብርና ሜካናይዜሽን እንዲስፋፋ በመንግሥት በኩል ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ ከመኾኑ ባሻገር ለዘርፉ ምቹ ሁኔታዎች መፈጠሩንም አስረድተዋል፡፡
ከነዚህ ውስጥ አንዱ የግብርና ሜካናይዜሽን ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ መደረጉ እና ከፋይናንስ ተቋማት ጋር በመቀናጀት የብድር ሥርዓት እንዲመቻች ከፍተኛ ጥረት መደረጉንም ገልጸዋል፡፡
በአርሶ አደሮች በኩልም ፍላጎት እንዲፈጠር እና እንዲቆጥቡ በማድረግ በመንግሥት በኩል የተፈጠሩ ምቹ ሁኔታዎችን መጠቀም እንደሚያስፈልግም ቢሮ ኀላፊው አሳስበዋል፡፡
የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን የግብርና ሜካናይዜሽንን ለማስፋፋት የክልሉ ግብርና ቢሮ በትኩረት እየሠራ ይገኛል ያሉት ኀላፊው የግብርና እና የገጠር ሽግግር እውን እንዲኾን የግብርና ሜካናይዜሽን መጠቀም ወቅቱ የሚጠይቀው ቁልፍ ተግባር ስለመኾኑ ጠቁመዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ሰናይት በየነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየአካባቢን ጸጋ በመለየት ማልማት ላይ መሪዎች ቀዳሚውን ሚና መወጣት አለባቸው።
Next articleግጭት ሕዝብን ያሰቃያል።