
ደብረ ብርሃን: ታኅሣሥ 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ሸዋ ዞን እና የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ሥልጠና ሲወስዱ የቆዩ መሪዎች በዞኑ እና በከተማ አሥተዳደሩ ሲከናወኑ የቆዩ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።
መሪዎች ከሥልጠና በኋላ የልማት ሥራዎችን መጎብኘታቸው በቀጣይ በአካባቢያቸው ለሚሠሩ የልማት ተግባራት የተሻለ ተሞክሮ ለማግኘት እንደሚረዳቸው ሃሳብ አንስተዋል።
ማኅበረሰቡን የሚጠቅሙ የልማት ተግባራትን ለመሥራት እና ባለሀብቶች በየአካባቢው እንዲመጡ ለማድረግ ጥረት እንደሚያደርጉ ሠልጣኞቹ ገልጸዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን አሥተዳደር ምክትል አሥተዳዳሪ ተክለየስ በለጠ በርካታ የሥራ ዕድል የፈጠሩ ፍብሪካዎችን መጎብኘታቸው ጠቀሜታው ከፍ ያለ መኾኑን ጠቅሰዋል።
ሠልጣኝ መሪዎች ወደ የመጡበት ሲመለሱ የአካባቢያቸውን ልማት በአግባቡ በማሥተዳደር ልማቱን እንዲያስቀጥሉ ተነሳሽነት ይፈጥራል ነው ያሉት።
ባለሃብቶች ወደ ሁሉም አካባቢዎች እንዲመጡ የተቀላጠፈ አገልግሎት መስጠትን ጨምሮ ያሉ “የአካባቢ ጸጋን በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባም” ገልጸዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ወርቃለማሁ ኮስትሬ መሪዎች በቀጣይ በሥልጠናው ያገኙትን አቅም ወደ ተግባር በመቀየር ማኅበረሰባቸውን መጥቀም እንደሚጠበቅባቸውም አስረድተዋል።
የብልጽግናውን ጉዞ ለማፋጠን በሚሠሩ ተግባራት ላይ መሪዎች የነቃ ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።
በዛሬው ዕለት ብራውን ዱቄት ፋብሪካ፣ የደብረ ብርሃን ከተማ ግብርና ምርምር ማዕከል እና ዴዴ ብርጭቆ ፋብሪካ ተጎብኝተዋል።
ዘጋቢ:- ስንታየሁ ኃይሉ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
