
ጎንደር: ታኅሣሥ 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የማዕከላዊ ጎንደር ዞን በወገራ ወረዳ የሰላም ጥሪውን ተቀብለው በምህረት ለገቡ አካላት” ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ መልዕክት ሥልጠና አስጀምሯል።
የወገራ ወረዳ አሥተዳዳሪ ሹመት ዋሴ በክልሉ ያለውን የሰላምን እጦት ለመቅረፍ የተደረገው ስምምነት ሁሉንም አሸናፊ ያደረገ ነው ብለዋል።
ግጭቱ በክልሉ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ጫና ያሳደረ መኾኑን ተናግረዋል። በምህረት የገቡ ታጣቂዎች በጫካ የሚገኙ ታጣቂዎችን በመምከር የሰላምን አማራጭ እንዲቀበሉ የበኩላቸውን እንዲወጡም መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመርሐ ግብሩ የተገኙት እና በሀገር መከላከያ ሠራዊት የሥራ ኀላፊ የኾኑት ኮሎኔል አዱኛ ማሞ የሰላም ስምምነቱን በመቀበል ፈር ቀዳጅ ኾነው መምጣታቸው ሊመሰገኑ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ግጭት እና መገዳደል ማብቃት እንዳለበት፣ የሰላምን አማራጭ በመቀበል ሀገርን ማልማት እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል። የሰላምን አማራጭ ሌሎች ታጣቂዎች እንዲቀበሉ እና ወደ ሰላም አማራጭ እንዲመጡ በጋራ መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አወቀ አስፈሬ ሥልጠናው ሰላምን በጋራ ለማጽናት የሚያስችል መኾኑን ተናግረዋል። በዞኑ አንጻራዊ ሰላም መኖሩን ገልጸው፤ ሰላም እንዲጸና የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት፤ የጸጥታ አካላት እና ማኅበረሰቡ ለከፈሉት ዋጋ አመስግነዋል።
በክልሉ የተደረገውን የሰላም ስምምነት በመቀበል የሰላም አማራጭን የተቀበሉ ታጣቂዎችን በማመስገን በውይይቱ የጋራ መግባባትን በመፍጠር በቀጣይ የአካባቢውን ሰላም ለማጽናት በትኩረት ልትሠሩ ይገባል ነው ያሉት።
ዞኑ የሰላም ጥሪ ለተቀበሉ አካላት የሥራ ዕድል በመፍጠር፤ ወደ ቀደመ ሥራቸው እንዲመለሱ በማድረግ የሕዝቡን ሰላም ለማረጋገጥ እንደሚሠራም ጠቁመዋል።
የሰላም አማራጭን የተቀበሉ ታጣቂዎች በቀጣይ ከሥልጠናው የሚያገኙትን ክህሎት በመጠቀም የማኅበረሰባቸውን ሰላም ለማጽናት በተግባር እንዲገልጡም ዋና አሥተዳዳሪው አሳስበዋል።
የሰላምን አማራጭ የተቀበሉ ታጣቂዎች በበኩላቸው የሰላም እጦቱ በክልሉ ሕዝብ ላይ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ጫና ማሳደሩን በመገንዘባቸው የሰላምን አማራጭ መቀበላቸውን አንስተዋል።
በቀጣይ በሥልጠናው የሚያገኙትን እውቀት ተጠቅመው ከመንግሥት ጋር በመኾን የአካባቢያቸውን ሰላም ለማጽናት እና በጫካ የሚገኙ አካላት ወደ ሰላም አማራጭ እንዲመጡ የበኩላቸውን ኀላፊነት እንደሚወጡም ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
