
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 17/2012 ዓ.ም (አብመድ) በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ሀገር ሊገቡ የነበሩ ቁሳቁስና አደንዛዥ እጾችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የኢፌዴሪ ገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቋል፡፡
ከሰኔ 11 እስከ 16/ 2012 ዓ.ም ድረስ ባሉት ስድስት ቀናት ውስጥ ግምታዊ ዋጋቸው ከ27 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የኮንትሮባንድ ዕቃዎችና የንግድ ማጭበርበር እንቅስቃሴዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
በሁሉም የጉምሩክ መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች በተደረገው ቁጥጥርና ፍተሻ ደግሞ የተለያዩ ዕቃዎች ላይ ሀሰተኛ ሰነድ በማቅረብና የተለያዩ ስልቶችን በመጠቀም የንግድ ማጭበርበር እንቅስቃሴዎችን የሚያደርጉ ህገ ወጦችን መቆጣጠር መቻሉን ነው ሚኒስቴሩ ያስታወቀው፡፡ በዚህም መንግሥት ሊያጣ የነበረው ከ9 ሚሊየን ብር በላይ ቀረጥና ታክስ እንዲከፈል መደረጉን ገልጧል፡፡
በቁጥጥር ስር ከዋሉ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መካከል የጉምሩክ ስነ-ስርዓት ሳይፈጸም ወደ ሀገር የገቡ ተሽከርካሪዎች፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ አልባሳት፣ የምግብ ዘይት እንዲሁም አደንዛዥ ዕፅና ሺሻ እንደሚገኙበት ታውቋል፡፡
