
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከታህሳስ 3 እስከ 6 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ የሚካሄደውን የልጅነት ልምሻ (ፖልዮ) መከላከያ ክትባት አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ ፖሊዮ እጅና እግርን ሽባ የሚያደርግ እና አለፍ ሲልም የሚገድል በሽታ መኾኑን ገልጸዋል።
ይህንን በሽታ ከሀገር ብሎም ከዓለም ለማጥፋት ጥረት እየተደረገ መኾኑን እና የአሁኑ ዘመቻም የዚሁ አካል መኾኑን ጠቅሰዋል።
ከዚህ በፊት ክትባቱ ይሰጥ የነበረው እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ለኾኑ ሕጻናት ነበር። አሁን ግን የበሽታው ምልክት ከአምስት ዓመት በላይ በኾኑ ሕጻናት ላይ መታየቱን ገልጸዋል።
በመኾኑም ክትባቱ በስምንት ዞኖች እና ከተማ አሥተዳደሮች (ሰሜን ጎጃም፣ ምሥራቅ ጎጃም፣ ደቡብ ጎንደር እና ማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች እና ባሕርዳር፣ ደብረታቦር፣ ደብረ ማርቆስ እና ጎንደር ከተሞች) እድሜያቸው ከአሥር ዓመት በታች ለኾኑ ሕጻናት ይሰጣል።
በቀሪዎቹ 14 ዞኖች እና ከተማ አሥተዳደሮች ደግሞ እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ለኾኑት ሕጻናት ይሰጣል ብለዋል።
ክትባቱ ቤት ለቤት፣ በትምህርት ቤቶች እና በመጠለያ ጣቢያዎች ይሰጣል።
በአጠቃላይ ከ5 ሚሊዮን በላይ ሕጻናት ክትባቱን ያገኛሉ ብለዋል።
በክትባት ዘመቻው ሌሎች የሕጻናት ክትባቶች እና የሕክምና አገልግሎቶችም እንደሚከወኑበት ተናግረዋል።
በዘመቻው ባለድርሻ አካላት፣ መንግሥት እና ኅብረተሰቡ በባለቤትነት ሊሠሩት እንደሚገባ አሳስበዋል።
ሕጻናት በብዛት የሚገኙባቸው ተቋማት እና ቤተሰቦች ሕጻናትን በማስከተብ መተባበር እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል።
ለተጨማሪ መረጃ በነጻ የስልክ መስመር 6981 ደውሎ መጠየቅ ይቻላል ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
