
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 1/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ “ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መልዕክት ሲከበር የቆየው 20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል የታለመለትን ዓላማ አሳክቶ መጠናቀቁን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር አስታወቁ።
አፈ ጉባኤው የበዓሉን ፍጻሜ አስመልከቶ በሰጡት መግለጫ መድረኩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ዕሴቶቻቸውን በመለዋወጥ ኅብረ ብሔራዊ አንድነታቸውን ይበልጥ ያጠናከሩበት እንደነበር ገልጸዋል።
ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በተከበሩ በዓላት ሕዝቦች ለረዥም ዘመናት ይዘውት የቆዩትን አብሮነት እና ወንድማማችነት እንዲያጠናክሩ፣ ከልዩነት ይልቅ አንድነትን እንዲያፀኑ፣ አስተናጋጅ ክልሎች ከፍተኛ የኾነ የገጽታ ግንባታ እና የኢኮኖሚ መነቃቃት እንዲፈጠሩ፣ በሕገ መንግሥቱ እና በፌዴራል ሥርዓቱ ዙሪያ ግንዛቤ እንዲያጎለብቱ እና ሀገራችን የምትከተለው የፌዴራል ሥርዓት በጥንካሬና በሰከነ መንገድ እንዲቀጥል የሚያስችሉ ሰፋፊ ሥራዎች ተሠርተዋል ብለዋል።
በፌዴሬሽን ምክር ቤት አሥተባባሪነት እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አስተናጋጅነት የተከበረው በዓል ቀዳሚ አብነት መኾኑን አመላክተዋል።
ከፌደሬሽን ምክር ቤት ማኅበራዊ ትስስር ገጽ እንዳገኘነው መረጃ ለበዓሉ በድምቀት መከበር አስተዋጽኦ ላበረከቱ የፌዴራል እና የክልል ተቋማት እንዲሁም እንግዳን በወንድማማችነት እና እህትማማችነት መንፈስ ለተቀበለው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሕዝብ ምሥጋና አቅርበዋል።
ቀጣዩ 21ኛው የብሔር፣ ብሔረሰቦች ቀን በጅማ ከተማ ይከበራል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
