የሕዳሴ ግድቡ ለቀጣናው ካለው ፋይዳ አንጻር ጎረቤት ሀገራት ድጋፋቸው ለኢትዮጵያ እንደሚሆን አቶ ገዱ አንዳርጋቸው አስገነዘቡ፡፡

176

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 17/2012 ዓ.ም (አብመድ) ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን ከግድቡ ጋር በተያያዘ ባደረጓቸው ድርድሮች የግብጽ ወገን የተለያዩ አጀንዳዎችን እያቀረበ ውይይቱን ውጤት አልባ ለማድረግ ተዘጋጅቶ ይመጣ እንደነበር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታና የሦስትዮሽ ድርድሩን በተመለከተ ከአልጄዚራ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልስ እንደገለጹት ግብጽ የራሷን ፍላጎት ብቻ ለመጫን ስትሠራ ነበር፡፡ በድርድሩ የግብጽ ወገን የተለያዩ አጀንዳዎችን እያቀረበ ውይይቱን ውጤት አልባ ለማድረግ ተዘጋጅቶ ይመጣ እንደነበርም ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

 

ግብጽ በጎረቤት አገሮች ላይ የጦር ሰፈር ለመመስረትና የኢትዮጵያን ደኅንነት ለመፈታተን የምታደርገውን ጥረት በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄም ሚኒስትሩ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ አቶ ገዱ በማብራሪያቸውም ግብጽ የተለያዩ ሙከራዎችን በመጠቀም ላይ መሆኗን፤ ነገር ግን ኢትዮጵያ ከሁሉም ጎረቤት ሀገራት ጋር ማለትም ከሱዳን፣ ከጅቡቲ፣ ከኬንያ፣ ከሶማሊያ፣ ከደቡብ ሱዳን እና ከኤርትራ ጋር ጠንካራ ግንኙነት ያላት በመሆኑ ሙከራው የማይሳካ ህልም መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ከዚህ ባለፈ የጎረቤት ሀገራት ግንኙነታቸውን በማጠናከር ወደ ኢኮኖሚያዊ ትስስር እና ውህደት እያመሩ በመሆኑ በዚህ ሁኔታ ሲመዘን ሀገራቱ ግብጽን በመደገፍ ኢትዮጵያን ለማጥቃት ይንቀሳቀሳሉ ብለው እንደማያምኑም አቶ ገዱ አንዳርጋቸው አስገንዝበዋል፡፡

 

በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል ያለው ግንኙነት ከመቼውም ጊዜ በተሻለ በከፍተኛ ደረጃ እየተጠናከረ እንደመጣ የገለጹት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከእርሻ መሬት ጋር በተያያዘ በድንበር አካበቢ የሚነሳው ችግር ለዘመናት የቆየ በመሆኑ ችግሩን በዘለቄታው ለመፍታት ሁለቱ አገራት በጋራ እና በትብብር እየሠሩ መሆኑንም አስረድተዋል። አብመድ ትናንት ባቀረበው ዘገባው የኬንያ ምሁራን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ለቀጣናው ልማትና ውህደት ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው፣ የቅኝ ግዛት ዘመናት ስምምነቶችም ፈጽሞ ተቀባይነት እንደሌላቸውና ቀጣናው ሀገራትም ከኢትዮጵያ ጎን መሆናቸውን መግለጻቸውን ማሳወቁ ይታዎሳል፡፡

 

በኢትዮጵያ እና በሱዳን ድንበር አካባቢ የተከሰተውን ሰሞነኛ ክስተት የግብጽ መገናኛ ብዙኃን እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም የሁለቱን አገራት ግንኙነት ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ እንዲያመራ በስፋት ሲሠሩ መቆየታቸውንም አብራርተዋል።

ግብጾች ግድቡን ከእስራኤል ጋር ለማገናኘት መሞከራቸው ስህተት ብቻ ሳይሆን ወንጀል መሆኑንም አቶ ገዱ ከጣቢያው ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡ ግብጽ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ እየተደረገ ያለው ድርድር እንዳይሳካ፣ የቅኝ ግዛት ዘመናት ውሎች ወደ ድርድሩ እንዲካተቱ ለማድረግ በተዘዋዋሪና በቀጥታ ፍላጎት በማሳየትና የተገፋች መስላ በመቅረብ የኢትዮጵያን ጥቅምና መብት ለመጋፋት አሉኝ የምትላቸውን ሁሉ አማራጮች እየተጠቀመች መሆኗ ይታወቃል፡፡

 

ከሀገራቱ ድጋፍ ለማግኘት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ እና በዲፕሎማቶቿ አማካኝነት ያደረገቻቸው ጥረቶችም ፍሬ እንዳላፈሩላት እየተነገረ ነው፡፡ ኢትዮጵያም ማንንም በማጎዳ መልኩ ሀብቷን የመጠቀም መብቷን ለማስከበር የማንንም ይሁንታ እንደማትጠብቅ በመግለጽ አቋሟን እያስረዳች ትገኛለች፡፡

 

በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡
Previous articleበኢትዮጵያ ተጨማሪ 185 ሰዎች የኮሮናቫይረስ ተገኘባቸው፡፡
Next articleከ27 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመቱ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መያዙን ሚኒስቴሩ ገለጸ፡፡