“መታከም ባለመቻሌ እግሬ ተቆርጧል፣ ዓይኔም ማየት አቁሟል” የሰላም እጦቱ ህክምና የነፈጋቸው አባት

6
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) መስከረም 01/2012 ዓ.ም የበዓል እርድ ለማድረግ ባጎነበሱበት ጊዜ ዓይናቸው ጨለመባቸው። ከዚያ ወዲህ ህመሙ እንዳለባቸው አውቀው ሕክምናውን እያገኙ ቆይተዋል።
ወደ ደብረ ታቦር እና ባሕር ዳር በመሄድም የሕክምና አገልግሎት ሲያገኙ ቆይተዋል።
አሁን ላይ ስኳር፣ ደም ግፊት እና ልብ ድካም በሽታ አለባቸው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት እንደልብ ተመላልሰው መታከም አልቻሉም።
ባሕር ዳር ፈለገ ሕይዎት ሆስፒታል ለነሐሴ 5/2017 ዓ.ም ቀጠሮ ቢሰጣቸውም ትራንስፖርት ባለመኖሩ ምክንያት በቀጠሯቸው አልተገኙም። ዘግይተው ቢቀርቡም ቀጠሮ በማሳለፋቸው ምክንያት መድኃኒቱ አልቋል ተባሉ።
እናም በበሽታ መደራረብ ችግር ውስጥ ገብተዋል። በአግባቡ ባለመታከማቸው ምክንያት በ2017 ዓ.ም አንድ እግራቸው ተቆርጧል። ዓይናቸውም ጠፍቷል።
አርሸ እና ነግጄ የምኖር ጀግና ነበርኩ ይላሉ አቶ መስፍን ዳኛው። በሕክምና እጦት ለጉዳት በመዳረጋቸውም በምሬት ውስጥ ናቸው፡፡ ለልጆቻችን ግን ቀን እንዲወጣላቸው መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የሰላም እጦቱ የሰዎችን ተዘዋውሮ የመሥራት እና የሸቀጦችን አቅርቦት ዝውውር ገድቧል። የባሰው ደግሞ የታመሙ ሰዎች ሕክምና በማጣት አካላቸው እየጎደለ እና እየሞቱ ነው።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በሰላም እጦት እና የመንገድ መዘጋት ለከፋ ጉዳት የተዳረጉትን ሰዎች ቤቱ ይቁጠረው።
ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ተሽከርካሪዎች መግባት አልቻሉም። በመኾኑም መድኃኒት የሚያጓጉዝ አይገኝም። በብዙ ጥረት የተጓጓዙትም ለዝርፊያ እና ለውድመት ይጋለጣሉ። በመኾኑም ተመላላሽ ታካሚዎች በቅርብ መድኃኒት ማግኘት አልቻሉም።
በችግሩ ምክንያት ሕዝቡ ለጊዜ፣ ለገንዘብ፣ ለጉልበት ብክነት ብሎም ለበሽታ መባባስ እና ለሞት እየተዳረገ መኾኑን መረዳት ይቻላል።
የደቡብ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ ኀላፊ ሙላቴ አሻግሬ በዞኑ ባለው ግጭት ምክንያት የጤና አገልግሎት ለመስጠት ችግሮች እንደሚያጋጥሙ ገልጸዋል።
አቶ ሙላቴ በግጭት አካባቢዎች የሚገኙ የሕክምና ባለሙያዎች ጫናውን ተቋቁመው እያገለገሉ መኾኑን ገልጸዋል። የሕክምና ግብዓት ለማቅረብ ግን የተሽከርካሪ እና የመድኃኒት አቅራቢው ድርጅትም ዝርፊያን በመስጋት ለመግባት መቸገራቸውን አብራርተዋል።
ስለኾነም መድኃኒት በሰው ሸክም እና በጋማ ከብት ለማድረስ እየተሞከረ መኾኑንም ገልጸዋል። ያም ኾኖ በቂ አልኾነም።
በችግሩ ምክንያት ሰዎች ሕክምና ሳያገኙ እንዳይቀሩ በዞኑ 16 ሺህ አባላት ያሉት 1 ሺህ 459 ኮሚቴ በጤና ኤክስቴንሽን አማካይነት የቤት ለቤት የጤና አገልግሎት እየተሰጠ ነው።
በዚህም ክትባቶችን፣ ወሊድን እና ተላላፊ ያልኾኑ ቋሚ በሽታ ያለባቸውን በማሰስ መድኃኒት እንዲያገኙ እና ሌሎች አገልግሎቶችም እየተሰጠ መኾኑን ነው አቶ ሙላቴ የተናገሩት።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኀላፊ አበበ ተምትሜ በክልሉ ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ አሁንም በቀጠለው ግጭት ምክንያት በጤና አገልግሎቱ ላይ ጫና መፈጠሩን ጠቅሰዋል፡፡
የግብዓት በወቅቱ አለመድረስ፣ መሰረቅ፣ የጤና ተቋማት እና የተሸከርካሪዎች እንዲሁም የመረጃ ሥርዓት መጎዳት እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች መኾቸውን ገልጸዋል፡፡
ለወረርሽኞች በተገቢው ሁኔታ ምላሽ ለመስጠት መቸገር እና የበሽታዎች ክስተት መኖሩንም ጠቅሰዋል፡፡
በክልሉ በተከሰተው ግጭት 960 ተቋማት ጉዳት እንደደረሰባቸው እና 92 ሚልዮን ብር የሚኾን የጤናው ዘርፍ ጉዳት እንደደረሰበትም ገልጸዋል፡፡ ችግሩን ተቋቁሞ ለመሥራት ማኅበረሰቡን እና አጋር አካላትን በማሥተባበር አገልግሎቱ መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡
ግብዓትን ተደራሽ ለማድረግ ተንቀሳቃሽ የሕክምና ቡድን በማዋቀር የጤና አገልግሎቱን ለማዳረስ እየተሠራ ነውም ብለዋል፡፡
ክትባት እና ሌሎችም ሕክምናዎችን በዘመቻ በመሥራት፣ ቀላል ጉዳቶችን በአጋር አካላት እንዲሟሉ በማድረግ፣ ማኅበረሰቡን በማሥተባበር እና የሕክምና አገልግሎቱ እንዳይቋረጥ እየተሠራ መኾኑንም አብራርተዋል፡፡
ዘጋቢ:- ዋሴ ባዬ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleሰላም ሁሉንም ተጠቃሚ እና ትርፋማ ታደርጋለች።
Next articleበግልፅ በመነጋገር ከተማዋ ወደ ቀደመ ሰላሟ እንድትመለስ እንሠራለን።