በምዕራብ ጎንደር ዞን የተፈጥሮ ሃብት ሥራ ተጀመረ።

10
ገንዳ ውኃ: ታኅሣሥ 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎንደር ዞን በ2018 ዓ.ም የተፈጥሮ ሃብት የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ልማት ሥራው በገንዳ ውኃ ከተማ ዙሪያ በፈንድቃ ተፋሰስ ተጀምሯል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ እያሱ ይላቅ የአካባቢውን ሰላም በማጽናት የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራዎችን በውጤታማነት ለማከናወን እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
ማኅበረሰቡ ሰላምን ከመጠበቅ ባሻገር የተፈጥሮ ሃብት ሥራውን በተጠናከረ መንገድ መሥራት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራን ማኅበረሰቡ በቅንጅት መሥራት እንዳለበት አሥተዳዳሪው መልዕክት አስተላልፈዋል።
በሀገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ የሥራ ኀላፊ የኾኑት ብርጋዴር ጄኔራል ቾምቤ ወርቁ ሠራዊቱ ሕግን ከማስከበር እና ሰላምን ከማስፈን ባሻገር በልማት ሥራዎች እየተሳተፈ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በቀጣይም በሚሠሩ የልማት ተግባራት ላይ ሠራዊቱ ተሳትፎውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና ግብርና መምሪያ ኀላፊ አንዳርጌ ጌጡ በ2017/18 በጀት ዓመት ከ140 በላይ ተፋሰሶችን ለመሥራት ታቅዶ ወደ ሥራ የተገባ መኾኑን ገልጸዋል።
በዛሬው ዕለት በማስጀመሪያው መርሐ ግብሩ በ67 ቀበሌዎች ከ110 በላይ የተፋሰስ ሥራዎች እየተሠሩ መኾቸውን አስረድተዋል።
በአዲስ 1ሺህ 400 ሄክታር መሬት እና በነባር 900 ሄክታር መሬት ላይ የተቀናጀ የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራ እንደሚከናወንም አብራርተዋል። በዚህ ዓመት በድግግሞሽ ከ36 ሺህ በላይ የማኅበረሰብ ክፍሎች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል ነው ያሉት።
የተሠሩ የተፋሰስ ተግባራት ተሠርተው ብቻ የሚተው ሳይኾን በየጊዜው አርሶ አደሮች ክትትል እንደሚያደርጉባቸውም ኀላፊው አስረድተዋል። የተፋሰስ ልማት ሥራው የተፈጥሮ ሚዛንን ለመጠበቅ እና የደን ሽፋንን ለመጨመር አይነተኛ ሚና አለው ብለዋል።
የተፋሰስ ልማት ሥራው ለ30 ተከታታይ ቀናት የሚቆይ መኾኑንም ኀላፊው ጠቁመዋል።
የገንዳ ውኃ ከተማ ዙሪያ ነዋሪው አርሶ አደር አየነው ያሲን የተፋሰስ ልማት ሥራዎች የአፈር ለምነትን በመጨመር ምርት እና ምርታማነት እንዲጨምር ያግዛል ነው ያሉት።
በተለይ በተፋሰስ ልማት ሥራው ለከብቶች መኖ የሚኾን ድርቆሽ እና የጥምር ግብርና ሥራዎችን ለመሥራት የሚጠቅም መኾኑንም አንስተዋል።
የተፋሰስ ልማት ተግባሩ የተራቆቱ አካባቢዎችን አረንጓዴ እንዲኾኑ እና አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ናቸው ያሉት ደግሞ አርሶ አደር የሱፍ ዳምጤ ናቸው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleከ2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ሰሊጥ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እየተሠራ ነው።
Next articleየምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ መልእክት፦