ከ2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ሰሊጥ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እየተሠራ ነው።

5
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ የቅባት እህሎችን በማምረት እና ወደ ውጭ በመላክ ከሚታወቁ አካባቢዎች ውስጥ የአማራ ክልል ከቀዳሚዎቹ ተርታ እንደሚቀመጥ የክልሉ ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ መረጃ ያሳያል።
የምርት አቅርቦቱ እና ግብይቱም እየተሻሻለ መምጣቱን ነው መረጃው የሚያሳየው። የግብይት ሥርዓቱም በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በኩል እንዲያልፍ ተደርጓል።
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ጎንደር ቅርንጫፍ ሥራ አሥኪያጅ ጥላሁን አስማረ እንዳሉት ምርት ገበያው የሰሊጥ ምርትን የጥራት ደረጃ በማውጣት ላኪዎች የሚፈለገውን ምርት ከምርት ገበያው እንዲያገኙ የማመቻቸት ሥራ እየሠራ ነው። በሻጭ እና ገዥው መካከል የሚደረገው ክፍያ በምርት ገበያው በኩል እንዲፈጸም እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
በዚህ መሠረት ምርት ገበያው በ2018 በጀት ዓመት 80 ሺህ ኩንታል ሰሊጥ ምርት ከአምራቹ በመሰብሰብ ለላኪዎች ለማስተላለፍ አቅዷል። እስከ አሁንም 35 ሺህ ኩንታል ወደ ምርት ገበያው መግባቱን ገልጸዋል። በዚህ ዓመት ከባለፈው ዓመት የተሻለ የምርት ጥራት መኖሩን ገልጸዋል። ለዚህ ደግሞ በ2017 ዓ.ም ደረጃ ሦሥት እና አራት የነበረው የሰሊጥ ምርት በዚህ ዓመት ወደ ደረጃ ሁለት እና ሦሥት ማደጉን በማሳያነት አንስተዋል።
የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ፈንታው ፈጠነ እንዳሉት የአማራ ክልል የቅባት እህሎችን በማምረት እና ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከሚታወቁ አካባቢዎች ውስጥ ዋነኛው ነው።
ክልሉ በ2017 በጀት ዓመት 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ሰሊጥ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ ከ2 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ኩንታል ማቅረብ ተችሏል ብለዋል።
በ2018 በጀት ዓመት ከ2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ሰሊጥ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። ከዚህም ከ333 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል። እስከ ኅዳር/2018 ዓ.ም 352 ሺህ ኩንታል ሰሊጥ ለውጭ ገበያ ማቅረብ መቻሉን ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱ ምርቱን ለውጭ ገበያ ከማቅረብ ባለፈ ከ108 ሺህ ኩንታል በላይ ሰሊጥ ተኪ ምርቶችን ለሚያመርቱ ፋብሪካዎች በግብዓትነት ለማቅረብ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። እስከዚህ ወቅት ከ58 ሺህ ኩንታል በላይ የሰሊጥ ምርት ማቅረብ መቻሉን ነው የገለጹት።
በኮምቦልቻ፣ ጎንደር እና ደብረ ማርቆስ በሚገኙ የኢትዮጵያ የምርት ገበያ ማዕከላት የሚዛን እና መጋዝን አገልግሎት እየተሠጠ መኾኑንም አንስተዋል።
ከሰሊጥ ባለፈ በክልሉ እንደ አኩሪ አተር፣ ማሾ፣ ቦሎቄ የመሳሰሉ ምርቶችንም ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
በዚህ ዓመት በየአካባቢው የሚመረቱ ምርቶች ከሌሎች አካባቢዎች ከተመረቱ ምርቶች ጋር ሳይደባለቁ ለውጭ ገበያ የማቅረብ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸውልናል። ይህም ምርቱ በተለይም ደግሞ እንደ ማሾ መሰል ምርቶች በዓለም ገበያ ተፈላጊ እንዲኾኑ አድርጓቸዋል ብለዋል።
በክልሉ የሚመረቱ የቅባት ምርቶች በዓለም ገበያ ተፈላጊነታቸውን ለማሳደግም ከእርሻ ቅድመ ዝግጅት ጀምሮ ሲሠራ መቆየቱን ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleሰብዓዊ መብትን ማክበር እና ማስከበር የሁሉም ኀላፊነት ነው።
Next articleበምዕራብ ጎንደር ዞን የተፈጥሮ ሃብት ሥራ ተጀመረ።