
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ቀን “ሰብዓዊ መብቶች፣ የዕለት ከዕለት ፍላጎቶቻችን” በሚል መሪ መልዕክት በአማራ ክልል ደረጃ በባሕር ዳር ከተማ ተከብሯል።
በመርሐ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሙሉዓለም ቢያዝን “ሰብዓዊ መብትን ማክበር እና ማስከበር የሁሉም አካላት ኀላፊነት ነው” ብለዋል።
በዓለም አቀፍ እና በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ድንጋጌዎች የሰብዓዊ መብት ከፍ ያለ ቦታ የተሰጠው እንደኾነ ገልጸዋል።
ሰብዓዊ መብት የሰው ልጅ በተፈጥሮ ያገኘው መብት በመኾኑ በሕግ አግባብ የተፈረደበት ካልኾነ በስተቀር የማይደፈር እና የማይገረሰስ ነው ብለዋል።
ሕግ አውጭ፤ ሕግ አሥፈጻሚ እና ሕግ ተርጓሚ አካላት ሰብዓዊ መብቶችን ማክበር እና ማስከበር ግዴታ የተጣለባቸው ስለመኾናቸውም ጠቁመዋል።
በተለይም ከሥራ ባሕሪያቸው አንጻር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው የፖሊስ፣ የፍትሕ እና የዳኝነት አካላት ከፍ ያለ ኀላፊነት ስላለባቸው በቁርጠኝነት ሊሠሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ማረሚያ ቤት መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር ተሻገር ባዬ የሰብዓዊ መብት ማንኛውም ሰው ሊነፈገው የማይገባ መብት በመኾኑ ሊጠበቅ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በሕግ ተፈርዶባቸው ወደ ማረሚያ ቤት የሚገቡ ታራሚዎችም ሰብዓዊ መብቶቻቸው ተከብሮላቸው እንዲኖሩ ማረሚያ ቤቶች ኀላፊነት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ሲያጋጥሙ ከማኅበረሰቡ ጋር በመተባበር ወደ ሕግ አካል ማቅረብ እንደሚገባ ጠቁመዋል። የቀኑ መከበርም ስለ ሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ግንዛቤን የሚፈጥር ስለመኾኑ ነው የተናገሩት።
ሌላኛው ተሳታፊ ባሮክ አማረ የሰብዓዊ መብት የእያንዳችን መብት በመኾኑ በሌሎች ላይ የሚያጋጥመውን የመብት ጥሰት በጋራ መከላከል ይገባል ባይ ናቸው።
የሰብዓዊ መብት የተጠበቀ የሚኾነው ሁሉም ተመሳሳይ ግንዛቤ ኖሮት በጋራ መከላከል ሲችል ነው ይላሉ።
በተለያዩ ምክንያቶች የሚፈጸሙ የሰብዓዊ ጥሰቶችን በመከላከልም ወጣቱ ትውልድ ግንባር ቀደም መኾን እንዳለበት ገልጸዋል።
በተለይም የፍትሕ አካላት የመብት ጥሰት ፈጻሚዎችን ወደ ሕግ በማቅረብ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ማድረግ እንደሚገባቸው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በዝግጅቱ የሰብዓዊ መብቶች አከባበርን በተመለከተ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጓል።
ዘጋቢ: አሰፋ ልጥገበው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
