
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 16/2012 ዓ.ም (አብመድ) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለቀጣናዊ ትብብር አስፈላጊ መሆኑን ኬንያውያን ምሁራን አስታውቀዋል፡፡
“ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለቀጣናዊ ልማት እና ውህደት ያለው ጠቀሜታ” በሚል ርዕስ በናይሮቢ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር በመተባበር ውይይት ተካሂዷል፡፡
በውይይቱ የተሳተፉ ኬንያውያን ምሁራንም ኢትዮጵያውያን የማንንም ፈቃድ እና ችሮታ ሳያስፈልጋቸው የራሳቸውን የተፈጥሮ ሀብት የማልማት መብት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ በቅኝ ግዛት ዘመን የተፈረሙ ስምምነቶች ተቀባይነት የሌላቸው እና ኋላ ቀር ሰነዶች መሆናቸውንም ምሁራኑ ማስረዳታቸውን በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታውቋል፡፡
የቅኝ ግዛት ዘመን ስምምነት ማንኛውም ሀገር የሚቀበለው አለመሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡ በመሆኑም በሕዳሴ ግድቡ ጉዳይ የቀጣናው ሀገራት ሕዝቦች ከአትዮጵያውያን ጋር መሆናቸውንና ኢትዮጵያ ብቻዋን አለመሆኗን አረጋግጠዋል፡፡
በውይይቱ በናይሮቢ ዪኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁራን፣ የቀድሞ የኬንያ ከፍተኛ የመንግስት ሥራ ኃላፊዎችና እና የቀጣናዊ ውህደት እና ልማት ጉዳዮች ተንታኝ አህመድ ሃሺ ተሳትፈዋል።
