“ዓይናችሁን ከዓላማችሁ ላይ አትንቀሉ” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)

21

ባሕር ዳር: ኅዳር 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት በምሥራቅ ጎጃም ዞን በመስክ ምልከታ የታዩ መልካም አጋጣሚዎች እና መፈታት የሚገባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ተካሂዷል።

በየደረጃው ለሚገኙ የሥራ ኀላፊዎችም የሥራ መመሪያ እና የቀጣይ አቅጣጫ ተቀምጧል።

የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) ባለፉት ዓመታት በተሠሩ ሥራዎች ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል። አሁን ላይ ማኅበረሰቡ ሰላም እንዲረጋገጥ ያሳየው ተነሳሽነት ለቀጣይ ሥራዎች መደላድልን የሚፈጥር ነው ብለዋል። በአካባቢው የነበረው የጸጥታ ችግር እየረገበ ወደ አንጻራዊ ሰላም መመለሱንም ሌላው ምቹ ሁኔታ ነው ብለዋል።

ያልተገሩ አስተሳሰቦች እና ለሕዝብ የማይጠቅሙ የትግል ስልቶች አሁንም ለሕዝብ ፈተና መኾናቸውን ተናግረዋል። መሪዎች የጠራ ሀሳብ መያዝ እና ማስያዝ እንደሚገባቸውም ገልጸዋል። መሪዎች ለሕዝብ አለኝታ መኾን፣ የመፍትሔ ሃሳብ ማመላከት፣ በአገልግሎት አሰጣጥ ሕዝብ እንዳይማረር ማድረግ ይገባቸዋል ነው ያሉት።

ሕዝብን ከችግር የማውጣት ታሪካዊ ኀላፊነት አለባችሁ ብለዋል። መሪዎች ሕዝብ በጽንፈኝነት አስተሳሰብ እንዳይጠለፍ መሥራት፣ ከሥነ ልቦና ጫና እንዲወጣ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል።

አካባቢውን በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሰላም መመለስ ከቻላችሁ ለሕዝብ ታሪካዊ ውለታ ነው የዋለችሁ ብለዋል። ሕዝብ በልማት እና በመልካም አሥተዳደር ሥራዎች እንዲረካ ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች በኢትዮጵያ የተሟላ ሰላም እንዳይኖር እንደሚሠሩም ገልጸዋል። ይህን በመረዳት ለሀገር ሰላም እና ልማት መሥራት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

ትልቅ ሕዝብ የምትመሩ ትልቆች ናችሁ፤ ከእናንተ ለትልቅነታችሁ የሚመጥን፣ ለሀገረ መንግሥት ግንባታው ሁነኛ ሚና የሚጫወት ተግባር ይጠበቃል ነው ያሉት።

የአማራ ክልል ሕዝብ ለሀገር ባለው አስተዋጽኦ ልክ አስተዋጽኦ እንዲያደርግ እና የሚገባውን እንዲያገኝ ከመሪዎች የሚጠበቅ ኀላፊነት እንዳለም አንስተዋል።

አካባቢውን በፍጥነት ሰላም በማድረግ ለልማት እና መልካም አሥተዳደር ሥራዎች ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል።

የሕዝብን እርካታ ከፍ የሚያደርጉ የልማት ሥራዎችን መሥራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል። መሪዎች ራሳቸውን ከሌብነት ማጽዳት እንዳለባቸው ያሳሰቡት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ሥርቆት ሰላምን የሚያውክ፣ ሕዝብን የሚያማርር፣ ክብርን እና ሀገርን የሚያሳጣ መጥፎ እሳቤ መኾኑን ተናግረዋል። ሕዝብን የሚያማርሩ ችግሮችን በፍጥነት እንዲፈቱም አሳስበዋል።

በፍጥነት መፍታት የማይችሉትን ደግሞ ከሕዝብ ጋር ተወያይተው መተማመን እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል። የሕግ የበላይነትን ማስከበር እና ወንጀልን መከላከል እንደሚጠበቅባቸውም አመላክተዋል። ጽንፈኛውን ከሕዝብ መነጠል እና ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚገባም ተናግረዋል።

የጸጥታ ኃይሉ ጽንፈኛው ያለበትን ቦታ እያሰሰ እንዲጸዳ ብቁ ድጋፍ እና አመራር መስጠት ያስፈልጋል ነው ያሉት። የጽንፈኛውን አቅም እና የአቅም ምንጭ ዜሮ ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል። ጽንፈኛው ቡድን አቅሙ እየደከመ እና እየፈራረሰ ነው፤ ይሄን አጋጣሚ በአግባቡ መጠቀም ይገባል ነው ያሉት።

ውጤታማ የሕዝብ ግንኙነት እና የፖለቲካ ሥራ እንዲሠሩም አስገንዝበዋል።

መሪዎች አሁን ያለውን ችግር መረዳት ይጠበቅባቸዋል ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ችግሩን በጥልቀት መረዳት፣ መተማመን እና ችግሩን በአጭር ጊዜ ለመፍታት በቁርጠኝነት መሥራት ይጠበቅባችኋል ነው ያሉት። “ዓይናችሁን ከዓላማችሁ ላይ አትንቀሉ”፣ በጥልቀት ተመልከቱ፣ ለዓላማ በጽናት ቁሙ ብለዋል።

ለሰላም እና ጸጥታ የቅድሚያ ቅድሚያ እንዲሰጡም አሳስበዋል። ከሕዝብ ጋር በጥልቀት መወያየት እና መግባባት ላይ መድረስ እንደሚገባም አንስተዋል።

ቅንጅትን እና ትብብርን በማጠናከር ሥራዎችን እንዲሠሩም አሳስበዋል። ሕዝብን ለሰላም እና ለልማት እንዲያነሳሱም አስገንዝበዋል ።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበከሚሴ ከተማ አሥተዳደር የተማሪዎች ምገባ ተጀመረ።
Next articleየግብፅ መሪዎች ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ለሥልጣን ማራዘሚያነት እየተጠቀሙበት ነው።