
ከሚሴ: ኅዳር 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር የከሚሴ ከተማ አሥተዳደር የተማሪዎችን ምገባ ማካሄድ ጀምሯል። በከተማ አሥተዳደሩ ቡኡረ ቦሩ ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ላይ ነው የምገባ መርሐ ግብሩ የተጀመረው።
በመርሐ ግብሩ የተማሪ ወላጅ የኾኑት ሼህ የሱፍ ይማም ለአሚኮ በሰጡት ሀሳብ የተማሪዎች ምገባን ከዚህ ቀደም በትላልቅ ከተሞች በሚዲያ ስንመለከት ነበር ብለዋል።
አሁን ላይ ወደኛ በመጣ ብለን ስንመኝ የነበረው ተግባር በከተማ አሥተዳደሩ መጀመሩ እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል።
በቀጣይ የምገባ መርሐ ግብሩ በሌሎች ትምህርት ቤቶችም እንዲሰፋ ሊሠራ ይገባልም ብለዋል።
ሌላዋ የከተማው ነዋሪ መዲና ሁሴን የምገባ መርሐ ግብሩ ወላጆችን ከሀሳብ የሚገላግል መኾኑን ገልጸዋል። ተማሪዎችም ጠንክረው እንዲማሩ ዕድል የሚፈጥር መኾኑን ተናግረዋል።
የከሚሴ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ሸሪፍ ቃሲም ከተማ አሥተዳደሩ የተሻለ ትውልድን ለመገንባት በማሰብ በጀት በመመደብ ከ2 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በቋሚነት ለመመገብ ወደ ሥራ መግባቱን ገልጸዋል።
በአሁኑ ሰዓት በቡኡረ ቦሩ ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከ400 በላይ ተማሪዎችን መመገብ መጀመሩን ጠቅሰዋል። በቀጣይ ቀናትም በሌሎች ትምህርት ቤቶችም ተግባሩ ይጀመራል ነው ያሉት።
በከተማ አሥተዳደሩ በርካታ ጫናዎችን ተቋቁመው ልጆቻቸውን የሚያስተምሩ ወላጆች በመኖራቸው ጫናውን ለማቃለል እና ለነገ የተሻለ ትውልድ ለመፍጠር በማሰብ ወደ ተግባሩ ከተማ አሥተዳደሩ መግባቱን ነው የተናገሩት።
የምገባ መርሐ ግብሩን በቀጣይ በሁሉም ትምህርት ቤት ለማስጀመር መታቀዱንም ከንቲባው ገልጸዋል። በዚህ ተግባር የከተማ አሥተዳደሩ ባለሀብቶች አሻራቸውን እንዲያሳርፉም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ:- ይማም ኢብራሒም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
