
ባሕር ዳር: ሕዳር 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት እና በአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) መካከል የተደረገውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በወገራ ወረዳና አካባቢው በተሳሳተ መንገድ ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ በርካታ ታጣቂዎች እየገቡ ነው።
በዛሬው እለትም በወገራ ወረዳና ኪንፋዝ ወረዳ አዋሳኝ ቀበሌዎች ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 35 ታጣቂዎች የሰላም ስምምነቱን መሰረት በማድረግ ገብተዋል።
በወገራ ወረዳ አምባ ጊወርጊስ ከተማ የገቡ ታጣቂዎችን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አወቀ አስፈሬ እና የዞኑ ፖሊስ መምርያ አዛዥ ኮማንደር ደሳለኝ አበራ በስፍራው ተገኝተው አቀባበል አድርገዋል።
በአቀባበሉ ላይ አቶ አወቀ አስፈሬ እንደገለጹት ከጦርነት ምንም ትርፍ እንደሌለ ተረድታቹህ የሰላም ስምምነቱን መሠረት በማድረግ መምጣታቹህ ለአካባቢያችሁ ሰላምና ልማት ያላቹህን ተነሳሽነት የሚያመላክት ነው ብለዋል።
በመንግሥት የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተረድተንና ተቀብለን በሰላም መግባት ችለናል ያሉት የቀድሞ ታጣቂዎቹ በቀጣይ የቀሩ ወንድሞቻችን የእኛን ፈለግ እንዲከተሉ በማድረግ ለአካባቢያችን ሰላምና እድገት የበኩላችን ለመወጣት ዝግጁ ነን ብለዋል።
በአቀባበሉ የዞኑ ዋና አሥተዳዳሪ አወቀ አስፈሬ እና የዞኑ ፖሊስ መምርያ አዛዥ ኮማንደር ደሳለኝ አበራን ጨምሮ የወረዳው አመራሮችና የመከላከያ ሠራዊት አመራሮች መገኘታቸውን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ኮሙኒኬሽን ያደረሰን መረጃ ያመለክታል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
