በሕዝቡ እና በአሥተዳደሩ ቅንጅት የመሠረተ ልማት ግንባታዎች እየተከናወኑ ነው።

10

ሁመራ፡ ኅዳር 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የውስጥ አቅምን በመጠቀም “በአንድ ወረዳ አንድ ፕሮጀክት” በሚል መነሻ እቅድ በዞኑ በርካታ የመንገድ እና ሌሎች መሠረተ ልማቶች እየተገነቡ ነው።

ከሰሞኑም በቃብትያ ሁመራ ወረዳ የቃብትያ – ሸሀሽም 10 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ ግንባታ ማስጀመሪያ ፕሮግራም ተከናውኗል።

የዞኑ ምክትል አሥተዳዳሪና የሰላምና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ መንገዱ በራስ አቅም እና ትብብር የሚሠራ መኾኑን አንስተው ለማጠናቀቅ ማኅበረሰቡ በንቃት እንዲሳተፍ ጠይቀዋል።

ከውስጥ በሚመነጭ ገንዘብ፣ የሰው ኀይል እና ሙያ ማኅበረሰቡ አካባቢውን እያለማ መኾኑን ያነሱት ኮልኔል ደመቀ በዚህም ፕርጀክቶችን ጀምሮ በአጭር ጊዜ ውስጥ የማጠናቀቅ እሴት እየተገነባ ነው ብለዋል።

ዞኑ ምንም እንኳ በጀት ባይኖረውም ሕዝቡን በማሳተፍ አካባቢውን ለማልማት እየተሠራ መሆኑን የተናገሩት የዞኑ መንገድ መምሪያ ኀላፊ ተመርጣ መብራቱ ናቸው። ከዚህ በፊት የተገነቡ የመንገድ መሰረተ ልማቶች የማኅበረሰቡን ጥያቄዎች በራስ አቅም መመለስ ያስቻሉ ናቸው ብለዋል፡፡

የተጀመረው የመንገድ ግንባታ የለውጡ ትሩፋት መኾኑን የተናገሩት የቃብትያ ሁመራ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ አታላይ ታፈረ መንገዱ የማኅበረሰቡ የረዥም ጊዜ ጥያቄ ነበር ብለዋል።

“ለውጡ ብዙ መስዋእት ተከፍሎበታል” ያሉት አቶ አታላይ ይሁን እንጂ በመስዋእትነት የተገኘው ነጻነት የዞኑ ሕዝብ ራሱን በራሱ እንዲያሥተዳድር እና አካባቢውን እንዲያለማ ማስቻሉንም አስረድተዋል።

አቶ አታላይ አክለውም መንገዱን ለመገንባት ከሀገር ውስጥ እስከ ውጭ የሚኖሩ ሀገር ወዳድ ወገኖች ድጋፍ እና ትብብር አስፈላጊ መኾኑን አንስተዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች በመንገድ አለመኖር ምክንያት ይቸገሩ እንደነበር አስታውሰዋል። ነዋሪዎቹ ችግሩን ለመቅረፍ በንቃት መሳተፍ እንደሚገባም ነው የተናገሩት።

መንገዱን በተያዘለት አራት ወራት ገንብቶ ለማጠናቀቅ የማኅበረሰቡ ሁሉን አቀፍ ትብብር እና ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ጥሪ ቀርቧል።

ዘጋቢ:- አምሳሉ አሞኘ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሴቶችን ጥቃት በጋራ መከላከል ያስፈልጋል።
Next articleበወገራ ወረዳና አካባቢው በተሳሳተ መንገድ ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን ተቀበሉ።