
ገንዳውኃ: ኅዳር 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎንደር ዞን የነጭ ሪቫን ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ34ኛ ጊዜ፣ በሀገራችን ደግሞ ለ20ኛ ጊዜ “ጥቃትን የማይታገስ ማኅበረሰብ ለትውልድ ግንባታ” በሚል መሪ መልዕክት በገንዳውኃ ከተማ ተከብሯል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ እያሱ ይላቅ በዓሉን ከማከብር ባለፈ የሴቶችን ጥቃት ለማስቆም የሁላችንን ኀላፊነት አለብን ብለዋል።
የሴቶች ጥቃት የእኔም ጥቃት ነው በማለት ጥቃቱን በጋራ መከላከል እንደሚገባ ዋና አሥተዳዳሪው አስገንዝበዋል።
በዞኑ ሴቶችን ወደ መሪነት ለማምጣት በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ አንስተዋል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ሴቶች ወጣቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ የሕፃናት መብትና ደኅንነት ቡድን መሪ መንግሥቱ ዓለማየሁ በዓሉ በዞኑ በሁሉም ወረዳ እና ከተማ አሥተዳደር ሲከበር ቆይቶ ዛሬ የማጠቃለያ በዓል መኾኑን አስታውሰዋል።
በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጫና ለመቀነስ እና ተሳትፏቸውንም ለማሳደግ ከአካባቢው ማኅበረሰብ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ተቋሙ በአጽንኦት እየሠራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
የበዓሉ ተሳታፊዋ ወይዘሮ ፋሲካ ሻንቆ የሴቶችን ጥቃት ለማስቆም ከንግግር ባለፈ እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ ግንዛቤ በመፍጠር ዜጎች በአስተሳሰብ እንዲቀየሩ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
ሌላኛው የበዓሉ ተሳታፊ አቶ ዮናስ አትክልት መጀመሪያ ከትምህርት ቤቶች አንስቶ እስከ ማኅበረሰቡ ድረስ የሴቶችን ግንዛቤ በማሳደግ ፆታዊ ጥቃትን በመከላከል ሴቶችን ወደ መሪነት እንዲመጡ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
