
ደብረ ማርቆስ: ኅዳር 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር “ትውልድን በሥነ ምግባር ተቋምን በአሠራር” በሚል መሪ መልዕክት 22ኛውን ዓለም አቀፍ የፀረ ሙስና ቀን አስመልክቶ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
በውይይት መድረኩ የሙስና ወንጀል አስከፊነትን በመረዳት በቁርጠኝነት መታገል የህልውና ጉዳይ መኾኑን የሚያመላክት ጽሑፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ፍትሕ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ንጉሴ ብናልፈው ከመሬት፣ ከግዥ እና ፍትሕ ሥርዓቱ ጋር ተያይዞ የሚታዩ ብልሹ አሠራሮችን እና የማይገባን ጥቅም ለማግኘት የሚፈጸሙ ድርጊቶች እንደ ከተማ ብቻ ሳይኾን እንደ ሀገር ከፍተኛ ቀውስ የሚያስከትሉ መኾናቸውን አብራርተዋል።
“አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ከእጅ መንሻ እና ከሙስና በጸዳ መልኩ የሚጠበቅባቸውን ኀላፊነት በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባም” አሳስበዋል ።
የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ኀብት ልማት መምሪያ ኀላፊ አየሁዓለም ያሳብ የሚሰጠው አገልግሎት ከችግር የጸዳ እና ተገልጋዮችን ያረካ ነው ባይባልም ብልሹ አሠራር በታየባቸው አንዳንድ አካላት ላይ እርምጃ መውሰድ ተጀምሯል ብለዋል።
አገልግሎት አሰጣጥ እና አሠራርን ማዘመን ጊዜው የሚጠይቀው ቁልፍ ጉዳይ ነው ያሉት ኀላፊዋ ለአገልግሎት አሰጣጥ ማነቆ የኾኑ ችግሮችን ለመቅረፍ የአንድ መሶብ ማዕከል አገልግሎትን ለማስጀመር የቅድመ ዝግጅት ተግባራት እየተከናወኑ መኾኑን ገልጸዋል።
መመሪያዎችን ሳይሸራርፉ በመተግበር እና ብቁ የኾኑ ባለሙያዎችን በሚገባቸው የሥራ መደብ ላይ በመመደብ ብልሹ አሠራርን አስቀድሞ መከላከል እንደሚገባ የውይይቱ ተሳታፊዎች አጽንኦት ሰጠው ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
