
ደሴ: ኅዳር 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በደቡብ ወሎ ዞን በሐይቅ ከተማ አሥተዳደር በወቅታዊ ሀገራዊና ክልላዊ የሰላምና የልማት ጉዳዮች ላይ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተወያይተዋል።
በውይይት መድረኩ ከደቡብ ወሎ ዞን ከሐይቅ ከተማ እና ከተሁለደሬ ወረዳ የተውጣጡ ልዩ ልዩ የኅብረተሠብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በአካባቢያቸው ዘላቂ ሰላም የሚሰፍንበትን ኹኔታ አመላክተዋል። የተለያዩ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችንም አቅርበዋል።
የአማራን ሕዝብ ነፃ እናወጣለን በሚል የተሳሳተ መንገድ ጫካ የገቡ ኀይሎች ክልሉን በሙሉ አቅሙ ወደ ልማት እንዳያተኩር አድርገውታል ብለዋል አስተያየት ሰጭዎች።
የታጠቁ እና ጫካ የገቡ ኀይሎች ተነሳንበት ከሚሉት ዓላማ በተቃራኒ ቆመው የታሪካዊ ጠላቶች ተልዕኮ ተሸካሚ በመኾን የባንዳነት ሥራ እየሠሩም ነው ብለዋል።
በጦርነት እና በግጭት ምክንያት ተጋላጭነታችን እና የሚደርስብን ጥቃት በእጅጉ ጨምሯል ብለዋል በምክክር መድረኩ የተሳተፉ ሴቶች።
በጫካ የሚገኙ አካላት ከእኛ የተሰወሩ አይደሉም ያሉት የውይይቱ ተሳታፊዎች
የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ሕዝቡን አስተባብረው እርቅ በማስፈን ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
በተለይ መንግሥት ለወጣቶች የሥራ እድል ልዩ ትኩረት በመስጠት የወጣቶችን ጥያቄ መመለስ እንደሚገባም ተመላክቷል።
የመንገድ፣ የውኃ፣ የመብራት እና ሌሎች የልማት ጥያቄዎችም እንዲመለሱላቸው ተሳታፊዎች ጠይቀዋል።
በሰሜኑ ጦርነት ጉዳት የደረሰበት እና የተቋረጠው የአዋሽ-ወልዲያ-ሃራ ገበያ የባቡር መንገድ እንዲኹም ግንባታው የተጓተተው የሐይቅ – ጭፍራ የአስፋልት መንገድ ግንባታ እንዲጠናቀቅም የውይይቱ ተሳታፊዎች አንስተዋል።
በአንዳንዳንድ ተቋማት የእጅ መንሻ የሚጠየቅባቸው አገልግሎቶች በመኖራቸው መንግሥት የአገልግሎት አሰጣጡን ሊፈትሽ እና መልካም አሥተዳደርን ሊያሰፍን እንደሚገባም ተጠይቋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን ባስተላለፉት መልዕክት ጫካ የገቡ የታጠቁ ኀይሎች የአማራ ሕዝብን አንገት የሚያስደፋ ተግባር እየፈፀሙ ነው ብለዋል።
ታጣቂዎች የሐይቅ ከተማ እና የተሁለደሬ ወረዳን ለማወክ ያላደረጉት ጥረት የለም ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው አመራሩ፣ ከጸጥታ መዋቅሩ እና ከሕዝቡ ጋር ማምከኑን አንስተዋል።
የብዙ ልማቶች መቋረጥ እና የመጓተታቸው ምክንያት የሰላም እጦት ነው ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው፣ የመልካም አሥተዳደር እና የልማት ጥያቄዎች በየደረጃው ምላሽ የሚያገኙት ሰላም ሲረጋገጥ ነው ብለዋል።
የተነሱ የልማት ጥያቄዎችን በየደረጃው ለመፍታት መንግሥት ይሠራል ያሉት አቶ አሊ ሐይቅ እና አካባቢውን የሚመጥኑ ሥራዎች እየተሠሩ በመኾኑ ኅብረተሰቡ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ፍስሀ ደሳለኝ በበኩላቸው ሐይቅ እና አካባቢው ሃይማኖቶች በጥበብ እና በአብሮነት የሚኖሩበት እንደኾነ አንስተዋል።
“አበጋር”ን የመሠለ የችግር መፍቻ ጥበብና እሴት የሚገኝበት አካባቢ በመኾኑ ግጭት እንዲቆም ልትሠሩበት ይገባል ብለዋል አቶ ፍስሀ።
ማኅበረሰቡ ማንንም ሳይጠብቅ ጫካ የገቡትን ወደ ሰላም አማራጭ ለመመለስ የሚደረገውን ጥረት እንዲደግፍም መክረዋል።
ከሕዝብ የተደበቀ ነገር ባለመኖሩ ታጣቂዎችን በትጥቅ፣ በመረጃ እና በስንቅ ባለማገዝ ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ፅጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ በተሁለደሬ ወረዳ እና በሐይቅ ከተማ አንፃራዊ ሰላም ይሰፍን ዘንድ ማኅበረሰቡ ያደረገውን አስተዋፅኦ አድንቀዋል።
የሀገራችን ቀዳሚ ፍላጎት ሰላምን ማፅናት ነው ያሉት አቶ ይርጋ “ኅብረተሰቡ በንቃትና በእኔነት ስሜት ያልተሳተፈበት ሰላም አይፀናም” ብለዋል።
በግጭት ውስጥ ዘመን ተሻጋሪ ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑን ያብራሩት አቶ ይርጋ ሐይቅ ከተማ የቱሪስት ማእከል እንደምትኾን ተስፋ ሰጭ ሥራዎች እየተሠሩ መኖራቸውን አንስተዋል።
ቱሪዝም ሰላም ይፈልጋልና ከመንግሥት ጎን በመሰለፍና ዘላቂ ሰላምን በማስፈን ከቱሪዝም ሃብት መጠቀም እንደሚገባ መክረዋል።
የአካባቢውን ሰላም በማፅናት ሂደት የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ያለመታከት እንዲሠሩ ጠይቀዋል አቶ ይርጋ።
የሰላም ጥሪውን ለመቀበል አሻፈረኝ ያሉ ታጣቂዎችን በሕግ ማስከበር ዘመቻው መልክ ለማስያዝ የሚደረገውን ጥረት ማገዝ ይገባልም ተብሏል።
ዘጋቢ:- ጀማል ይማም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
