የመታመን ዋጋው ከ8 ነጥብ 4 ሚልየን ብር በላይ ሲሆን!

21

ባሕር ዳር: ኅዳር 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ነገሩ እንዲህ ነው ኅዳር 13 ቀን 2018 ዓ.ም ከቀኑ 5፡15 ሰዓት ላይ ወደ ንግድ ባንክ አካውንታቸው 8 ነጥብ 4 ሚልዮን ብር እንደገባላቸው ማሳወቂያ (ኖትፊኬሽን) ደረሳቸው፡፡ ግራ የገባቸው ግለሰቡ ሁኔታውን ለጓደኞቻቸው ነገሩ።

ከዚህም አልፈው በአካባቢው ለሚገኘው የንግድ ባንክ ቤዛዊት ቅርንጫፍ፣ ለባሕር ዳር ከተማ ፖሊስ ዋና መምሪያ እና ለጣቢያኛ ጣቢያ አመለከቱ፡፡ እኝህ ሰው ቻላቸው ጌጡ የተባሉ እና በአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ባለሙያ ናቸው፡፡

ፖሊስ ጉዳዩን አጣርቶ አካውንቱ እንዳይንቀሳቀስ ተደረገ፤ ከወንጀል ነጻ መኾኑንም አረጋገጠ፡፡ ጉዳዩ ተጣርቶ ከአዋሽ ባንክ በስህተት እንደተላለፈ ተነገረኝ ብለዋል አቶ ቻላቸው፡፡ “ሰው የሰውን አንገት ጠምዝዞ ይሰርቃል፤ ራሱ የመጣን ሲሳይ እንዴት ትመልሳለህ?” ዓይነት ቀልዶችም እንዳጋጠሟቸው ተናግረዋል።

በስህተት የገባው ገንዘብ ኅዳር 29 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚመለስ እንደተነገራቸው ጠቅሰዋል፡፡ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቤዛዊት ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ ይህዓለም አድማሱ አቶ ቻላቸው በስህተት የገባላቸውን ገንዘብ በታማኝነት መመለሳቸውን አረጋግጠዋል፡፡

የአዋሽ ባንክ ደንበኛ የኾነ አንድ ግለሰብ በአዋሽ ባንክ በኩል ወደ ሌላ ባንክ ገንዘብ ለማስገባት ፈልጎ ነገር ግን በስህተት ወደ አቶ ቻላቸው ጥሩነህ አካውንት መግባቱ ተረጋግጧል፡፡ ፖሊስም ገንዘቡ በስህተት የተዘዋወረ እንጂ የወንጀል አለመኾኑን ስላረጋገጠ ገንዘቡ ኅዳር 29 ቀን 2018 ዓ.ም ወደ ባለቤቱ መመለሱን ተናግረዋል፡፡

አቶ ቻላቸውም ላላቸው ታማኝነት እና መልካም ሥነ ምግባር የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም የምስጋና እና እውቅና ደብዳቤ ጽፎላቸዋል፡፡ “8 ነጥብ 4 ሚልዮን ብር ብዙ ነው፤ አቶ ቻላቸውን ግን አላታለላቸውም” ነው ያሉት የንግድ ባንኩ ሥራ አስኪያጅ፡፡

በተመሳሳይ በስህተት 127 ሺህ ብር የገባለት ግለሰብ ብሩን ላለመመለስ ብዙ አስቸግሮ እንደነበር አስታውሰው አቶ ቻላቸው ግን 8 ነጥብ 4 ሚልዮን ብርን ያለ ምንም ውጣ ውረድ በቅንነት መመለሳቸውን ጠቅሰው ነው ያደነቁት፡፡

“እንኳን አገኘሁ ብሎ ገንዘቡን የሚያጠፋ እና የሚያሸሽ ሰው ባለበት ዘመን የአቶ ቻላቸው ታማኝነት ግን የሚደንቅ እና የሚያስመሰግናቸው ነው” ብለዋል፡፡

ዘጋቢ:- ዋሴ ባዬ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እንዲያድግ ከተፈለገ ተቋማትን በቴክኖሎጂ ማዘመን ይገባል” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
Next articleየቋሚ ቅጥር ማስታወቂያ