
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 16/2012 ዓ.ም (አብመድ) ቶኒ ሁጄል የተባለ የአምስት ዓመት አካል ጉዳተኛ ታዳጊ 10 ኪሎ ሜትር በመጓዝ ድጋፍ ለማሰባሰብ ያቀደውን በእጥፍ ማሳካቱ ተዘግቧል፡፡
ታዳጊው በወላጆቹ በተፈፀመበት ድብደባ ለአካል ጉዳት ተዳርጎ ከሌሎች አሳዳጊዎች ጋር ነው የሚኖረው፡፡ በተፈፀመበት ድብደባ ምክንያት ሁለቱም እግሮቹ በሕክምና ተቆርጠዋል፤ በአጋዥ መሳሪያዎች እየተረዳም ነው የሚንቀሳቀሰው፡፡ ይህ ታዳጊ መሰል ጥቃት የደረሰባቸውና ሰው ሠራሽ መንቀሳቀሻ ለሚሹ ታዳጊዎች ለሕክምና ወጭ የሚሆን ገንዘብ ለመሰብሰብ በአውሮፓውያኑ ሰኔ ወሩን ሙሉ የ10 ኪሎ ሜትር ጉዞ በማድረግ ግማሽ ሚሊዮን ፓውንድ ለመሰብሰብ አቀደ፡፡ የሳምንት ጊዜ እየቀረው ታዲያ 1 ሚሊዮን 14 ሺህ 348 ፓውንድ ድጋፍ በማሰባቡ በደስታ ፈንድቋል፡፡
የተሰበሰበው ገንዘብ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው በትክክል መድረሱንም ኤቩሊና ለንደን የተባለው የሕጻናት ሆስፒታል አረጋግጧል፡፡ የታዳጊው ቶኒ አሳዳጊ ‘‘በደስታ ሰክሬያለሁ፤ የሆነውን ለመግለጽም ቃላት የሉኝም፤ እውነት መሆኑን ሁሉ ማመን ከብዶኛል’’ በማለት ለቢቢሲ ተናግረዋል፡፡ ታዳጊው ድጋፉን ለማሰባሰብ የወሰነው በካፒቴን ቶም ሙሬ ተግባር ተነሳስቶ ነው፡፡ ካፒቴን ቶም ሙሬ የቀድሞ የእንግሊዝ የጦር ጀት አብራሪ የ100 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ ናቸው፡፡
በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ችግር ውስጥ ያሉትን የእንግሊዝ የጤና ባለሙያዎች ለማገዝ በቅርቡ 100ኛ ዓመት ልደታቸውን ምክንያት በማድረግ በግቢያቸው ውስጥ የ10 ኪሎ ሜትር የእግር ጉዞ በማድረግ የገንዘብ ማሰበሳበ ዕቅድ አወጡ፡፡ በዕቅዳቸው መሠረት 1000 ፓውንድ ለመሰብሰብ እንቅስቃሴ ጀመሩ፤ በኋላ ግን ከጠበቁት በብዙ እጥፍ የሆነ 32 ሚሊዮን 794 ሺህ 701 ፓውንድ መሰብሰብ ቻሉ፤ ይህም ለታዳጊው መልካምነትን አስተማረ፤ ተምሮም ወደ ተግባር ለወጠው፡፡
የመልካም አሳቢው ታዳጊ አሳዳጊ እስከ 8 ሺህ 300 ሜትር ጉዞ ማድረጉን ለቢቢሲ ገልጸዋል፡፡ በተገኘው ስኬት ቤተሰቡ መደሰቱንና በታዳጊው ልጃቸው እንደኮሩ ተናግረዋል፡፡ ታዳጊው ቀሪ ኪሎ ሜትሮችንም በቀሪ ቀናት እንደሚያጠናቅቅና ተጨማሪ ገንዘብ እንደሚያገኝም ይጠበቃል፡፡ በጎ ፈቃደኛው በስኬቱ ከፍተኛ የደስታ ስሜት ላይ መሆኑንም አሳዳጊው ተናግረዋል፡፡
የሆስፒታሉ የገቢ ማፈላለግ ተባባሪ ዳይሬክተር ‘‘በታዳጊው ተግባርና ልግስና ተደምመናል፤ ያሰባሰበው ገንዘብ እንደ እርሱ ላሉ ታዳጊዎች ሕክምና የሚውልም ይሆናል’’ ብለዋል፡፡ እንደ ቢቢሲ ዘገባ የእግር ጉዞው ለታዳጊው ትልቅ የራስ መተማመንም ፈጥሮለታል፡፡
በአብርሃም በዕውቀት
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡
