
ባሕር ዳር: ኅዳር 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከጤና ቢሮ፣ ከዩኒሴፍ፣ ከዓለም ጤና ድርጅት እና ሌሎች አጋር አካላት ጋር በመተባበር ክልላዊ የተቀናጀ የፖሊዮ በሽታ መከላከያ ክትባት ዘመቻ የንቅናቄ መድረክ አካሂዷል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ዋና ጸሐፊ እና የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አባል መላዕከ ብርሃን ፍስሐ ጥላሁን ክልሉ በተለያዩ ምክንያቶች መጎዳቱን ጠቅሰው በጤናው ዘርፍም ጉዳት እንደደረሰበት ገልጸዋል፡፡
ሕጻናት በጤና አድገው ሀገር እንዲረከቡ ጤናቸውን መጠበቅ እና መንከባከብ ተገቢ ነው ብለዋል።
ክትባቱ ውጤታማ እንዲኾን ባለድርሻ አካላት እና ወላጆች ትኩረት እንዲሰጡ አሳስበዋል፡፡ የጤና ባለሙዎች የሚመክሩትን የፖሊዮ በሽታ መከላከል ሥራም ከሃይማኖት የማይቃረን መኾኑን ገልጸዋል፡፡
የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሼህ ሙሐመድ ኢብራሒም የፖሊዮ መከላከያ ክትባት በእስልምና ሃይማኖት ዘንድ ቅቡልነት ያለው መኾኑን ገልጸዋል።
የሕጻናትን ሕይዎት በመታደግ አምራች ትውልድን ማስቀጠል እንደሚገባም ተናግረዋል።
በሽታን መከላከል ነፍስን ማትረፍ ነው፤ ሁላችንም ለክትባቱ በባለቤትነት ማስተባበር ይገባልም ብለዋል፡፡
በአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከል እና መቆጣጠር ባለሙያ ቢንያም ከበደ ከታኅሣሥ 3 እስከ 6/2018 ዓ.ም የሚካሄደው የፖሊዮ መከላከያ ክትባት ለአራተኛ ጊዜ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
ባለፉት አምስት ዓመታት በክልሉ 12 የፖሊዮ በሽታ ምልክቶች በመገኘታቸው ምክንያት ክትባቱን እንደገና መስጠት እንዳስፈለገ ነው የገለጹት፡፡
ዕድሜው ከአምስት ዓመት በላይ በኾነ ሰው ላይ የፖሊዮ በሽታ በመገኘቱ ክትባቱ የሚሰጠው ከአሥር ዓመት በታች ለኾናቸው ሕጻናት ሁሉ ነው ብለዋል፡፡
ክትባቱ ከአሥር ዓመት በታች ለኾኑት የሚሰጠው በሥምንት ዞኖች እና ከተማ አሥተዳደሮች እንደኾነም ገልጸዋል፡፡ በ14 ዞኖች እና ከተማ አሥተዳደሮች ደግሞ ዕድሜያቸው ከአምሥት ዓመት በታች ለኾናቸው ነው ብለዋል፡፡
የመድኃኒት፣ የባለሙያ እና የግንዛቤ ፈጠራ ዝግጅት ተጠናቋልም ነው ያሉት፡፡
የክትባቱ ዘመቻ ቤት ለቤት ስለኾነ ለሕጻናት የመደበኛ ክትባት እና የበሽታ ቅኝት እና አሰሳ እንደሚሠራም ገልጸዋል፡፡
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኀላፊ አበበ ተምትሜ በውይይቱ ባስተላለፉት መልዕክት በክልሉ የሕጻናትን ሕይዎት ለመታደግ ከጽንሰት እስከ ውልደት እና እድገት ድረስ ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
የፖሊዮ በሽታን ለመከላከል እና ለማጥፋት ትልቅ ሥራ እንደሚጠይቅ ገልጸው በሀገር ደረጃ ለማጥፋት ለሚደረገው ጥረት ኅብረተሰቡ እና አጋር አካላት ትብብር እንዲያደርጉም አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ:- ዋሴ ባዬ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
