‎የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ (አዴኃን) ሦስተኛ መደበኛ ጉባኤውን አስመልክቶ መግለጫ ሰጠ፡፡

39
ባሕር ዳር: ኅዳር 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ (አዴኃን) ሦስተኛ መደበኛ ጉባኤውን አካሂዷል። ጉባኤውን አስመልክቶም ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።
የአዴኃን የጥናት እና ምርምር ኀላፊ አዲሱ ጉልላት (ዶ.ር) ድርጅቱ ባካሄደው ጉባኤ የአማራ ሕዝብ የጸጥታ ችግሮችን በዝርዝር ተወያይቶባቸዋል ብለዋል፡፡
‎በተለይም አሁን ባለው የክልሉ ወቅታዊ የጸጥታ ችግር ምክንያት ሕጻናት ከትምህርት ገበታ እንዲቀሩ ማድረጉ፣ የጤና ተቋማት በሙሉ አቅማቸው አገልግሎት እየሰጡ እንዳልኾና አሁን ያለው የጸጥታ ሁኔታ ለወንጀለኞች እና ሥርዓት አልበኝነት ሕዝቡን ተጋላጭ እያደረገው መኾኑን አባላቱ እንደመከረበት ገልጸዋል፡፡
‎ድርጅቱ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት እና በሰላማዊ ትግል መፍትሔ በማፈላለግ በኩል የመፍትሔ አካል ኾኖ ለመሥራት አቋም ተይዟል ብለዋል፡፡
‎ወደፊት የክልሉ ሕዝብ ከጸጥታ ችግር ወጥቶ ልጆቹን የሚያስተምርበት፣ የሕግ የበላይነት የሚከበርበት እና ሰላም ተፈጥሮለት የሚኖርበትን ሁኔታ ለመፍጠር በሚያስፈለጉ የመፍትሔ ሃሳቦች ላይ በመምከር አቋም ተይዟል ነው ያሉት፡፡
‎የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ራስወርቅ መላኩ ለሁለት ቀናት በቆየው ጉባኤ ዓለም አቀፍ፣ ሀገር አቀፍ፣ ክልል አቀፍ እና የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ ሁኔታ ላይ በሰፊው እንደተወያዩበት ተናግረዋል፡፡
‎ጉባኤው ስኬታማ እና አዲስ የሰው ኃይል እና መሪዎች ወደ ድርጅቱ የመጡበት ነውም ብለዋል፡፡ በአዲስ ፊት፣ በተጠናከረ እና ወቅቱን በሚመጥን ክልላዊ እና ሀገራዊ የአመራር ሂደት ውስጥ ከፍ ያለ ሚና ለመጫወት በሚያስችል ሁኔታ የሥራ አሥፈጻሚው እና የማዕከላዊ ኮሚቴው የተዋቀረበት እንደኾነ ነው የገለጹት።
‎አዴኃን በትጥቅ ትግል እና በሰላማዊ ትግል የተፈተነ ድርጅት በመኾኑ ከግጭት ያለውን ጉዳት፣ ከሰላም የሚገኘውን ጠንቅቆ የሚያውቅ በመኾኑ የዚህ ድርጅት ተጠናክሮ መውጣት በተለይም ለአማራ ሕዝብ ሰፊ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ነው ያሉት፡፡
‎በክልሉ የሰላም ሁኔታ በመንግሥት እና በታጠቁ ኃይሎች መካከል ያለው ግጭት በውይይት እና በድርድር እንዲሁም በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ በሁለቱም አካላት የሚደረገውን የሰላም ጥረት ይደግፋል ብለዋል፡፡
‎እየተሰቃየ እና እየተንገላታ ያለውን ማኅበረሰብ ሰላሙን ለማረጋገጥ አዴኃን የበኩሉን ሚና መጫወት እንዳለበት የጉኤው ተሳታፊዎች በአጽንኦት አንስተዋል ነው ያሉት፡፡
‎በጉባኤው ማጠቃለያም አቶ ተስፋሁን አለምነህን የድርጅቱ ሊቀመንበር፣ አዳነ ወዳጀነህ (ዶ.ር) ምክትል ሊቀመንበር፣ አቶ ራስወርቅ መላኩ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ፣ አዲሱ ጉልላት (ዶ.ር) የጥናት እና ምርምር ኀላፊ እንዲሁም ሌሎች ዘጠኝ የሥራ አሥፈጻሚዎችን እና 29 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ተመርጠዋል ብለዋል፡፡
‎የድርጅቱ ጉባኤ ተሳታፊዎች በክልሉ በሁሉም ቦታዎች በመንቀሳቀስ እና አባላትን በመመልመል ከነበረው በበለጠ ለክልሉ ሕዝብ ጠበቃ እና ደጀን እንዲሁም አሸናፊ ፓርቲ ኾኖ ለመውጣት እና ለሕዝብ የበለጠ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱበትን ሁኔታ በመወያየት ጉባኤው መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡
‎ዘጋቢ፡- ፍሬሕይወት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleከአስከፊ ግጭት ፈጥኖ መውጣት ለነገ የማይባል ተግባር ነው።
Next articleፖሊዮን ለማጥፋት በሚደረገው ጥረት ኅብረተሰቡ ትብብር እንዲያደርግ ተጠየቀ።