
ደሴ፡ ኅዳር 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች የተመራ ልዑክ በደቡብ ወሎ ዞን ለጋምቦ ወረዳ በወቅታዊ፣ ክልላዊ እና ሀገራዊ የሠላም እና የልማት ጉዳዬች ላይ ከተለያዩ የኀብረተሰብ ክፍሎች ጋር መክረዋል።
በውይይት መድረኩ ከወረዳው፣ ከፊጣ እና ከቀይ መብራት አካባቢዎች የተውጣጡ ልዩ ልዩ የኀብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።
የውይይት መድረኩ በመዘጋጀቱ ያመሰገኑት ተሳታፊዎች የሰላም እጦቱ እረፍት አልባ ሕይዎት እንዲገፉ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል።
የአማራን ሕዝብ ነፃ እናወጣለን በሚል የተሳሳተ መንገድ ጫካ የገቡ ኃይሎች የተነሱበት ዓላማ በርካቶችን አሳስቷል ብለዋል አስተያየት ሰጭዎች። እያደር ዓላማቸው ተገልጦልናል፤ ግድያ እና ዝርፊያ የዘወትር ሥራቸው ኾኗል ብለዋል።
ወንድም ወንድሙን የሚገድልበት አስከፊ ግጭት በኛ ዘመን በማየታችን አፍረናል ነው ያሉት።
ልጆቻችን ትምህርት ናፍቋቸዋል፤ እኛም በሰላም ወጥቶ ለመግባት ተቸግረናል ብለዋል አስተያየት ሰጭዎች።
የክልላችን ብሎም የወረዳዎች ሰላም የሚረጋገጠው ሁላችንም የሰላም ዘብ ስንኾን ነው ያሉት አስተያየት ሰጭዎች በኋላ ይበቃናል ብለዋል።
በጫካ የሚገኙ አካላት ከሕዝብ የተሰወሩ አይደሉም ያሉት የውይይቱ ተሳታፊዎች የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች እርቅ በማስፈን ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
የተጀመረውን የሰላም ስምምነት እንደመልካም አጋጣሚ ተጠቅመው ለዘላቂ ሰላም እንዲሰሩም ተጠይቋል።
የአካባቢው ማኀበረሰብ ከልብ የመነጨ የሰላም ማስፈን ሥራ ሊሠራ እንደሚገባም ነው የተመላከተው።
በተለይ መንግሥት ለሥራ እድል ልዩ ትኩረት በመስጠት የወጣቶችን ጥያቄ መመለስ እንደሚገባም ተጠይቋል። የመንገድ፣ የመብራት፣ የጤና ተቋማት እና የንፁህ መጠጥ ውኃና ሌሎች የልማት ጥያቄዎችም እንዲመለሱላቸው ተሳታፊዎች ጠይቀዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን በመድረኩ ባስተላለፉት መልእክት ጫካ የገቡ አካላት ለሀገረ መንግሥት ግንባታ የላቀ ሚና ያለውን የአማራ ሕዝብ አንገት የሚያስደፋ ተግባር እየፈፀሙ ነው ብለዋል። ክልሉን በሁለንተናዊ መልኩ ለማዳከም ተላላኪ እና ተልዕኮ ተሸካሚ በመኾን የባንዳነት ሥራ እየሠሩም ነውም ብለዋል።
የብዙ ልማቶቻችን መስተጓጎል ምክንያቱ የሰላም እጦት ነው ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው የመልካም አሥተዳደር እና የልማት ጥያቄዎች በየደረጃው ምላሽ የሚያገኙት ሰላም ሲፀና እንደኾነ በአጽንኦት ተናግረዋል።
በብልፅግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ፍሰሃ ደሳለኝ የጥፋት ቡድኑ ዓላማም፣ መዳረሻ፣ ግብም የለውም ብለዋል።
የሰላም ጥሪ ከቤተሰብ ይጀምራል ያሉት አቶ ፍሰሀ ማኅበረሰቡ ማንንም ሳይጠብቅ ጫካ የገቡትን ወደ ሰላም አማራጭ ሊመልስ እንደሚገባ መክረዋል።
በመንግሥት በኩል ለሰላም የተዘረጉ እጆች አለመታጠፋቸውንም አንስተዋል።
በብልፅግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ በአካባቢው አንፃራዊ ሰላም ይሰፍን ዘንድ ማኅበረሰቡ ያደረገውን አስተዋፅኦ አድንቀዋል።
የሀገራችን እና የክልላችን ቀዳሚ ፍላጎት ሠላምን ማፅናት ነው ያሉት አቶ ይርጋ ክልሉን ገጥሞት የቆየው ችግር በታሪካችን አስከፊው ነው ብለዋል።
ከአስከፊው ችግር በአፋጣኝ መውጣት ደግሞ
ለነገ የማያድር ሥራ መኾኑን ነው ያስገነዘቡት።
የለጋምቦ ወረዳና የአካባቢው ማኀበረሰብ በሙሉ አቅም መሪዎችን እና የፀጥታ መዋቅሩን በመደገፍ የታየውን አንፃራዊ ሠላም ዘላቂ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ ጀማል ይማም
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
