
ባሕር ዳር: ኅዳር 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል መንግሥት እና በአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) መካከል የተደረገውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በወገራ ወረዳ እና አካባቢው በጫካ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች የመንግሥትን የሰላም አማራጭ ተቀብለዋል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አወቀ አስፈሬ የመንግሥትን የሰላም አማራጭ ለተቀበሉ አካላት አቀባበል አድርገውላቸዋል።
የሰላም አማራጩን የተቀበሉ አካላት በአማራ ክልል መንግሥት እና በአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) መካከል የተደረገውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ እንደገቡ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ እንድትበታተን ከሚፈልጉ ኃይሎች ጋር የሚደረግ ግንኙነት አጥፊ በመኾኑ ሰላምን መርጠን መጥተናል ብለዋል።
በቀጣይ የሕዝባችን ሰላም እና ልማት እንዲረጋገጥ ከመንግሥት ጎን ኾነን እንሠራለን ነው ያሉት።
ሰላምን አስቀድማችሁ መምጣታችሁ ለሕዝባችሁ እና ለሀገራችሁ ያላችሁን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ያሉት የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አወቀ አስፈሬ ናቸው።
የአማራን ሕዝብ ጥያቄ በብጥብጥ እና በጦርነት ሳይኾን በሰላማዊ እና በዴሞክራሲያዊ አኳኋን ለመፍታት መሞከር ተገቢ መኾኑንም አንስተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
