
ባሕር ዳር: ኅዳር 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የተቋማት የሕዝብ ግንኙነት፣ የሚዲያ እና የኮሙዩኒኬሽን መሪዎች በባሕር ዳር ከተማ የሚገኘውን የአማራ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪ እና ማሽን ቴክኖሎጂ ልማት ኢንተርፕራይዝ ፋብሪካን ጎብኝተዋል። ተቋሙ እያከናወናቸው በሚገኙት ተግባራት ዙሪያም ውይይት ተደርጓል።
በጉብኝቱ ያገኘናቸው የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ አስማረች ምስክር ኢንተርፕራይዙ የክልሉን ችግር ከመቅረፍ ባለፈ እንደ ሀገርም ተወዳዳሪ ለመኾን የሚያስችለውን ሥራ እያከናወነ እንደሚገኝ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የሚያመርታቸው ምርቶች ለኮሪደር ልማት ግብዓት በማቅረብም የራሱን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተናግረዋል። የኢንተርፕራይዙ ምርቶች ለማኅበረሰቡ ተደራሽ እንዲኾኑ ግዛቤ በመፍጠር የበኩላቸውን እንደሚወጡም ገልጸዋል።
የአማራ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪ እና ማሽን ቴክኖሎጂ ልማት ኢንተርፕራይዝ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ዘላለም በላይ ኢንተርፕራይዙ የክልሉን የግብርና እና የአምራች ኢንዱስትሪውን የቴክኖሎጂ ፍላጎት ለማሟላት ዓላማ አድርጎ እየሠራ ነው ብለዋል።
በአነስተኛ እና በመካከለኛ ደረጃ የሚሠሩ የፋብሪካ ማሽኖችን የማምረት ተልዕኮ ይዞ ከውጭ የሚገቡ ማሽኖችን ለመተካት ትኩረት አድርጎ እየሠራ ስለመኾኑም ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅት ለኮሪደር ልማት ሥራዎች የሚውሉ ግብዓቶችን እያመረተ እንደሚገኝም ገልጸዋል። በፋብሪካው ውስጥ የሚገኘው የብረት ማቅለጫ ኢንዱስትሪ በቀን እስከ 96 ቶን የሚደርስ ብረት የማቅለጥ አቅም አለው ነው ያሉት።
ለውኃ ፓምፕ እና ለአሲዳማ አፈር ማከሚያ ግብዓት ማምረቻ የፋብሪካ ማሽነሪዎችን ለማቅረብም እየተሠራ ነው ብለዋል። በሁለት ወራት ውስጥ 50 የሚኾኑ የላይም ስቶን ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን አምርቶ ለገበያ እንደሚያቀርብም ጠቁመዋል።
በሰዓት 30 ኩንታል መኖ ማምረት የሚያስችሉ የመኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን በማምረት በሁሉም ወረዳዎች ለማዳረስ እየተሠራ ስለመኾኑም አንስተዋል። የሚያመርታቸውን ምርቶች ለገበያ ለማቅረብ የገበያ ችግር እያጋጠመ በመኾኑ ትስስር እንዲፈጠር ጠይቀዋል።
የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኅላፊ ዓባይ መንግሥቴ ኢንተርፕራይዙ መዋቅራዊ ሽግግርን እውን ለማድረግ የሚያግዝ ተቋም መኾኑን አንስተዋል። የብረታ ብረት እና የግንባታ ግብዓቶችን በማምረት የውጭ ምንዛሬን ለማስቀረት እንደሚያግዝም ተናግረዋል።
በግንባታው እና በግብርናው ዘርፍ ለሚፈለገው እድገት ተስፋ የሚሰጥ ስለመኾኑም አብራርተዋል። ወደ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለሚደረገው ሽግግርም ሚናው የጎላ ነው ብለዋል።
የገበያ ትስስር ችግሩን ለመፍታት የትውውቅ ሥራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አስገንዝበዋል። ኅብረተሰቡም ለሀገር ውስጥ ምርቶች ትኩረት እንዲሰጥ አስገንዝበዋል።
የሚዲያ እና የሕዝብ ግንኙነት አካላትም በማስተዋወቅ በኩል ሚናቸውን መወጣት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
ዘጋቢ: አሰፋ ልጥገበው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
