“ፖሊስ የተሟላ የሚኾነው ፖሊሳዊ፣ ሀገራዊ፣ ቀጣናዊ፣ አሕጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ዕውቀቶች ሲኖሩት ነው” ምክትል ርእሰ መሥተዳደር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)

11
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ለጎጃም ቀጣና ፖሊስ መሪዎች እና አባላት በተቋማዊ ሪፎርም፣ ጅኦ-ስትራቴጂ እና በፖሊስ አመራር ጉዳዮች ዙሪያ በደብረ ማርቆስ ከተማ ሥልጠና እየተሰጠ ነው።
ሥልጠናው በአማራ ክልል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ነው እየተሰጠ የሚገኘው።
በሥልጠና ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት ምክትል ርእሰ መሥተዳደር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አስተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር) እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ፕሬዝዳንት ምክትል ኮሚሽነር አበበ ደለለ የአማራ ክልል ፖሊስ ከሌሎች የጸጥታ ኃይሎች ጋር በመኾን በክልሉ የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር ለመቀልበስ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ሌት ተቀን ሠርቷል ብለዋል። በሠራው ሥራም አንጻራዊ ሰላም እንዲመጣ አድርጓል ነው ያሉት።
በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ከሚሰጡ መደበኛ ሥልጠናዎች በተጨማሪ አጫጭር የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን በማዘጋጀት የተጀመረውን የሪፎርም እና ለውጥ ጎዞ መሬት ለማድረስ እና የአባላትን እና የመሪዎችን የመፈጸም አቅም ለማሳዳግ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል። የዛሬው ሥልጠና የዚሁ አካል መኾኑን ተናግረዋል።
ይህ ሥልጠና የፖሊስ መሪዎች እና አባላት የሚሰጣቸውን ግዳጅ በብቃት እና በስኬታማነት ለመፈጸም፣ የተጀመረውን የሕግ ማስከበር ተግባር በውጤታማነት ለማጠናቀቅ የሚያስችል ቁመናን የሚፈጥር ነው ብለዋል።
የፖሊስ ሪፎርማችን እና የተቋማችንን የከፍታ ጉዞ በመረዳት ቀጣይነት ያለው የፖሊስ አገልግሎትን ለሕዝባችን ለመስጠት እና ሀገራችን ያለችበትን ጅኦ-ስትራቴጅካዊ ቁመና ላይ የተሻለ ግንዛቤ ለመፍጠር ያስችላል ነው ያሉት።
ለተግባራዊነቱ እንደ ፖሊስ የሚጠበቅብንን ተልዕኮ ለመወጣት የሚያስችል ሥልጠና ነው ብለዋል።
በሥልጠናው የሪፎርም ጽንሰ ሃሳብ፣ የሪፎርም አተገባበር፣ የዲጅታል አመራር ልማት፣ ተቋማዊ ግንባታ፣ ሀገር ወዳድነት እና የኢትዮጵያን ጅኦ-ስትቲጀካዊ ሁኔታዎች እና ሌሎች ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮች እንደሚሠጡ ተናግረዋል።
ሥልጠናው ያሉብንን ክፍተቶች የምንፈትሽበት፤ ወቅታዊ እና ሀገራዊ ጉዳዮችን የምንረዳበት፣ እርስ በርስ ልምድና ተሞክሮ የምንለዋወጥበት ነው ብለዋል። ሥልጠናው ለቀጣይ ሥራቸው ከፍተኛ የኾነ መነሳሳት እና የተሻለ አቅም የሚፈጥር ነው ብለዋል።
የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ተሾመ ዋለ ሥልጠናው ብቁ መሪዎች እና አባላት እንዲፈጠሩ የሚያስችል ነው ብለዋል። ሥልጠናው በስኬት እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉም አስታውቀዋል።
የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳደር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) የአማራ ክልል ፖሊስ ወደ ቀደመ እሴቱ፣ ክብሩ እና አቋሙ እየተመለሰ መኾኑን ተናግረዋል። የቀደው ክብር እና እሴት ተጠብቆ እንዲቀጥል በትኩረት እንዲሠሩም አሳስበዋል።
ተቋማዊ ሪፎርም እና የጂኦ ስትራቴጂ ሥልጠናዎች ለፖለስ መሪዎች እና አባላት ወሳኝ ነው ብለዋል። ሀገራችሁን በጀግንነት ለመጠበቅ፣ ሕዝባችሁን በሰብዓዊነት ለማገልገል፣ የኢትዮጵያን ጠላቶች ማንነት እና አሰላለፍ ማወቅ ይገባችኋል ነው ያሉት።
የጂኦስትራቴጂ ሥልጠና የኢትዮጵያ ጠላቶችን ማንነት እና አሰላለፍ በመረዳት ፖሊስ ሚናውን እና ተልዕኮውን ለመወጣት ያስችላል ነው ያሉት።
ፖሊስ የጂኦስትራቴጂ ሥልጠና ሲወስድ ለቀጣናው የኃይል አሠላለፍ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ እና ምላሽ መስጠት እንደሚችል ተናግረዋል። የኢትዮጵያን የጂኦ ስትራቴጂ ጥቅም ለማዛባት የሚሠሩ የኃይል አሠላለፎችን ቀድሞ ለመከላከል እና ለመመከት እንደሚያስችም ገልጸዋል።
የጂኦፖለቲካዊ እና ጂኦስትራቴጂውን የተረዳ ፖሊስ እና የፖሊስ ተቋም መገንባት እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል። የጂኦ ስትራቴጂካዊ ጥቅም የሚያሳጣ ወንጀል እንዳይከሰት መከላከል፣ መመከት እና ከተከሰተም በአፋጣኝ በመቀልበስ ዳግም እንዳይከሰት አስተማሪ እርምጃ ለመውሰድ ፖሊስ በጂኢስትራቴጂ ጉዳዮች ብቁ መኾን እንዳለበት አመላክተዋል።
ፖሊሳዊ ዕውቀትን የተላበሰ ምርምራ እና እርምጃ በመውሰድ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ እንደሚገባም ተናግረዋል። “ፖሊስ የተሟላ የሚኾነው ፖሊሳዊ፣ ሀገራዊ፣ ቀጣናዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ዕውቀቶች ሲኖሩት ነው” ብለዋል። እነዚህ ዕውቀቶች ሲኖሩት የሀገርን ሰላም እና ደኅንነት ያስጠብቃል፤ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ያሳካል ነው ያሉት።
የአማራ ክልል መንግሥት የፖሊስ ተቋሙ ሪፎርም እንዲያደርግ በወሰነው ውሳኔ መሠረት አመርቂ ውጤት ተገኝቷል ብለዋል። ተቀዛቅዞ የነበረው ፖሊሳዊ እሴት፣ ክብር እና የግዳጅ አፈጻጸም ብቃት ተመልሷል ነው ያሉት። ግዳጅ የመወጣት ብቃቱ ከፍ ማለቱን ተናግረዋል። የፖሊስ ተቋሙ ገለልተኝነት፣ ተቋማዊ ነጻነት፣ እሴት እና ክብሩ መመለሱንም አንስተዋል።
የተጀመረው ሥልጠና እስካሁን ካላቸው ዕውቀት ላይ ተጨማሪ ዕውቀት የሚሰጥ፣ በጂኦስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያለውን የባንዳ እና የባዕዳ አሰላለፍ ለማወቅ የሚያስችል መኾኑን ተናግረዋል።
ጂኦስትራቴጂካዊ አሰላለፉን ተረድተው የሕዝብን ሰላም እና ደኅንነት እንዲያረጋግጡም አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleለጸጥታ ኃይሎች አጋዥ በመኾን ሰላምን ዘላቂ ማድረግ የሁሉም ኀላፊነት ነው።
Next articleየአማራ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪ እና ማሽን ቴክኖሎጂ ልማት ኢንተርፕራይዝ መዋቅራዊ ሽግግርን እውን ለማድረግ የሚያግዝ ነው።