
በአማራ ክልል ሰኔ 15/2011 ዓ.ም የተሰው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና የፀጥታ አካላት መታሰቢያ አንደኛ ዓመት የፓናል ውይይት ትናንት በባሕር ዳር ተካሄዷል፡፡
በፓናል ውይይቱ የተሳተፉ የተቋማት የሥራ ኃላፊዎች እና የማኅበረሰብ ተወካዮች ድርጊቱ ሁሉንም ያሳፈረ በመሆኑ ሁሉም ተምሮበት በአንድነት በመቆም የሕዝቡን መሠረታዊ ጥያቄዎች እንዲመለሱ የሚሠራበት ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የሰማዕታትን ዓላማ ማሳካት የሚቻለው ትምህርት ቤቶች የፈጠራ ማዕከል ሲሆኑ፣ በወሊድ ምክንያት የሚሞቱ እናቶች እንዳይኖሩ ሲደረግ መሆኑን የውይይቱ ተሳታፊዎች አመልክተዋል፡፡ የፀጥታ አካላትን ሰማዕትነት መመለስ የሚቻለው ደግሞ የአማራ ክልል የኢንቨስትመንት እና የቱሪዝም ማዕከል እንዲሆን ሰላማዊ ቀጠናን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እና በአንድነት መሥራት ሲቻል መሆኑ ተናግረዋል፡፡
ከተሳታፉዎች መካከል አቶ ወርቅነህ እንደግ ‘‘ለሕዝቦች ሰላምና አንድነት ለማስፈን መሥዋዕት የሆኑ መሪዎችን ዓላማ የምናሳካው የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎችን በጋራ አመራር የሚፈጽም የሥራ ኃላፊ ሲፈጠር ነው’’ ብለዋል፡፡
የአማራ ሕዝብን ጥቅምና ማንነት የሚጸረሩ ኃይሎችን ጉልበት እና አቅም ማሳጣት የሚቻለው በአንድነት የሰማዕታቱን ግብ ማሳካት ሲቻል እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
አሁን ያሉ የሥራ ኃለፊዎች የተሰው የሥራ ኃላፊዎችን ዓላማ ለማሳካት በድርጊቱ ከመከፋፈል ይልቅ በአንድነት እና በቁርጠኛ መሥራት እንዳለባቸው ያሳሰቡት ደግሞ አቶ እንድሪስ አብዱ ናቸው፡፡
ወይዘሮ ከድጃ ያሲን ደግሞ ‘‘ሰማዕቶቹ ለሕዝብ ጥቅም ከከፈሉት መሥዋዕትነት እና የዓላማ ጽናት በመማር አዲሱን ሰኔ 15 ለዕድገት መስፈንጠሪያ አድርጎ መጠቀም ያስፈልጋል’’ ብለዋል፡፡
ሌላኛው የፓናል ውይይቱ ተሳታፊ አቶ ቤንጃሚን ወንዴ ‘‘ከሰማዕቶቹ የምንማረው ለዓላማ መሥራትንና ለዓላማ መሞትን ነው፡፡ የአማራ ሕዝብ ከድርጊቱ በአንድነት በመቆም ጸረ ሰላም ኃይሎችን በመታገል እና ልማት በሚያሳልጡ ተግባራት ላይ አሻራውን በማስቀጠል ሊያስባቸው ይገባል’’ ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ግርማ ተጫነ
