
ደብረ ማርቆስ: ኅዳር 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ደጃዝማች ተድላ ጓሉ ክፍለ ከተማ” ዘካሪ እና መካሪ ኅብረተሰብ ለዘላቂ ሰላም እና ልማት” በሚል መሪ መልዕክት ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት ተደርጓል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በከተማው እየተገነቡ ያሉ የመሠረተ ልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡ የሰላም ዘላቂነት የሚመጣው በመመካከር እና በመነጋገር በመኾኑ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ አበባው ግዛቸው የተጀመሩ ልማቶች እንዲቀጥሉ እና የማኅበረሰቡ የልማት ጥያቄዎች እንዲፈቱ ለሰላም ቅድሚያ መስጠት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
ሁሉም ማኅበረሰብ የበኩሉን ድርሻ ሊያበረክት ይገባልም ብለዋል። የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ላቀች ሰማ በየአካባቢው ያለውን ሰላም በመደራጀት መጠበቅ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ከእርስ በርስ መጠፋፋት ወጥተን ችግሮችን በውይይት እና በምክክር መፍታት ይገባል ነው ያሉት፡፡ “ለጸጥታ ኃይሎች አጋዥ በመኾን ሰላምን ዘላቂ ማድረግ የሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ኀላፊነት እንደኾነም” ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
