
ባሕር ዳር: ኅዳር 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 20ኛው የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን “ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ መልዕክት የማጠቃለያ መርሐ ግብር በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ እየተካሄደ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እና የሀገሪቱ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በበዓሉ ታድመዋል። መልዕክት ያስተላለፉት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርእሰ መሥተዳድር እንደሻው ጣሰው (ዶ.ር) ኢትዮጵያ በልዩ ልዩ እምርታዎች ታጅባ ለምናከብረው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል።
“የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ይህን ታላቅ ሀገራዊ በዓል እንዲያዘጋጅ ስለተሰጠን ዕድለኞች ነን፤ በዓሉ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በተለያዩ ቦታዎች ሲከበር ቆይቷል” ነው ያሉት። የልዩነት መነሻ በኾኑ ታላላቅ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ዜጎች መክረው እና ዘክረው የመፍትሔ አካል ለመኾን የጋራ ትርክትን መሠረት ለማኖር እና የሀገረ መንግሥቱን ቅቡልነት ለማስቀጠል ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተግባር ተጠናክሮ በቀጠለበት በዚህ ጊዜ እየተከበረ የሚገኘው በዓሉ ምክክሩ ውጤታማ እንዲኾን አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝቦች በአንድ መድረክ ተገናኝተው እንዲደምቁ በዓሉ መሠረታዊ ነው ብለዋል። በዓሉ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ባሕላቸውን እና ልምዳቸውን እንድለዋወጡ ዕድል የፈጠረ እንደኾነም ነው የገለጹት።
ለወንድማማችነት እና እህትማማችነት እሴቶች ማበብም ሚናው የጎላ እንደኾነ ነው የገለጹት።
“በዓሉ ለጋራ ትርክት ግንባታ አስተዋጽኦው ሰፊ እንደኾነ ነው” የተናገሩት። ቀኑ ሲከበር ለሀገራዊ ክብር ቅድሚያ በመስጠት የመመካከር እና የመወያየት ባሕልን በማላቅ መኾን እንዳለበት ርእሰ መሥተዳድር እንደሻው ጣሰው ተናግረዋል።
“የዘንድሮው በዓል የዘመናት ቁጭት መቋጫ፤ የአዲስ ንጋት ማብሰሪያ፤ የማንሰራራት ዘመን ምልክት የኾነውን የሕዳሴ ግድብ መርቀን እና ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በተበሰረበት ጊዜ መኾኑ ልዩ ያደርገዋል ነው” ያሉት።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ከመላው ኢትዮጵያውያን ጋር በፍቅር እና በአንድነት የዘለቁ ሥለመኾናቸውም አንስተዋል። ሕዝቦቹ የተሻለ የሥራ ባሕል ያላቸው እንደኾኑም ገልጸዋል።
ኅብረ ብሔራዊት ኢትዮጵ ያን በመገንባት ረገድም የራሳቸውን አሻራ ያሳረፉ ሕዝቦች ስለመኾናቸውም ተናግረዋል። ትጋታቸውንም በቀጣይነት አጠናክረው ይቀጥላሉ ነው ያሉት።
ጠንካራ ኢትዮጵያን እውን በማድረግ ሂደት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ሚና ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል ዶክተር እንደሻው ጣሰው በመልዕክታቸው።
ዘጋቢ፦ ሰለሞን አንዳርጌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
