
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 16/2012 ዓ.ም (አብመድ) የታች ጋይንት ወረዳ ነዋሪዎች ሰኔ 15/2011 ዓ.ም ለሕዝባቸው መራራ መሥዋዕትነት የከፈሉ መሪዎችን እና ከእነርሱ ጎን በመሆን የተሰው የፀጥታ ኃይል አባላትን ክብራቸውን ለመግለጽ እና መታሰቢያም ይሆናቸው ዘንድ የተለያዩ ተግባራትን አከናውነዋል። በተለያዩ ቀበሌዎች የሚኖሩ አርሶ አደሮች ‘‘ችግራችንን በራሳችን አቅም እንፈታለን’’ በሚል 40 ኪሎ ሜትር የሚረዝም መንገድ በራሳቸው ገንዘብ ሠራተዋል። እያንዳንዱ ቤተሰብ ለመንገዱ ማሠሪያ አቅም በፈቀደ መጠን ገንዘብ ማዋጣቱን በወረዳው አብመድ ያነጋገራቸው የአቄቶ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
አርሶ አደሮቹ እንዳሉት መራራ መሥዋዕትነትን ለከፈሉ የቀድሞ የአማራ ክልል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ኅብረተሰቡ የተለያዩ ማኅበራዊ ልማቶችን እያከናወነ ይገኛል። ከነዚህም መካከል ከፍተኛ ችግር የሆነባቸውን መንገድ መራሳቸው አቅም መሥራት አንዱ ነው። በቻሉት አቅም እና ባላቸው ገንዘብ የመጀመሪያ ጥርጊያ መንገድ አሠርተዋል። ነገር ግን ጠጠር ካልተደፋበት ገንዘብ እና ድካማቸው ከንቱ እንዳይቀር ከፍተኛ ስጋት አላቸው።
“ኅብረተሰቡ ያቅሙን ያክል ሠርቷል” ያሉት አርሶ አደሮቹ የተሠራው መንገድ በውኃ ሳይታጠብ ቢቻል አስፓልት ካልሆነም ደግሞ ጠጠር እንዲያለብስላቸው ጠይቀዋል። ከሕዝቡ አቅም በላይ የሆኑ ድልድዮችን እንዲሥሩላቸውም ጠይቀዋል።
የመንገድ ችግር ከፍተኛ ፈተና ነበረባቸው፣ ወላዶች ወደ ሕክምና ተቋም ለመድረስ በመንገድ ችግር እንግልት ይገጥማቸዋል፤ ሌሎች ሕሙማንንም ወደ ጤና ተቋም ለማድረስም ከፍተኛ ችግር ነበረባቸው። የዚህ መንገድ መሠራት እነዚህን ችግሮች እንደሚቀርፍላቸው የተናገሩት አርሶ አደሮቹ የሕዝብ ትራንስፖርት እንዲመደብላቸውም ጠይቀዋል። መንግሥት ከዚህ ቀደም ቃል ገብቶ ያልሠራቸውን መንገዶች እንዲሠራም ጠይቀዋል።
የታች ጋይንት ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ ደስታው ገላው እንዳሉት ማኅበረሰቡ ሰማዕታቱን ለማሰብ በርካታ ሥራዎችን ሠርቷል። ትምህርት ቤቶችን መገንባት፣ የነባር ትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሳደግ፣ በክልሉ እና በዞኑ ተጀምረው የተቋረጡ የውኃ ግንባታዎችን ማጠናቀቅና አገልግሎት እንዲሰጡ ማደረግ በኅብረተሰቡ ከተከናወኑ የልማት ሥራዎች ተጠቃሾች እንደሆኑ አስታውቀዋል። በተለይም የዘመናት ጥያቄ የነበረውን የመንገድ መሠረተ ልማት በራሳቸው አቅም ለመሥራት ልዩ ትኩረት ሰጥተው እንደተንቀሳቀሱ አቶ ደስታው ተናግረዋል። በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥም 40 ኪሎ ሜትር የሚጠጋ መንገድ መሥራታቸውን ተናግረዋል። መንገዱ ሲሠራ መንግሥት ለአርሶ አደሮች የመሬት ካሳ በመክፈል እና ባለሙያዎችን በመመደብ ድጋፍ ማድረጉንና ቀሪው ሥራ በአርሶ አደሮች የተሸፈነ መሆኑን አመልክተዋል።
የወረዳው መንግሥት ለማሽን ነዳጅ እና ለሠራተኛ ክፍያ ገንዘብ መመደቡን የተናገሩት አቶ ደስታው ክረምት ገብቶ መንገዱ ለብልሽት ሳይጋለጥ ለማስተካከል ሁኔታዎች እየተመቻቹ መሆኑንም ተናግረዋል። የዞኑ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የተከናወኑ ሥራዎችን መጎብኘታቸውም ጥያቄዎቹ ምላሽ እንዲያገኙ ዞኑም ድጋፍ እንዲያደርግ እንደሚያስችል ጠቁመዋል። የዓርብ ገበያ አቄቶ የሕዝብ ትራንስፖርት ይመደብልን ጥያቄ ሌሎች ሥራዎች ከተጠናቀቁ በኋላ ምላሽ እንደሚሰጠውም ቃል ገብተዋል።
መንገዱ ትናንት በዞንና በወረዳ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች መጎብኘቱ የሚታወስ ነው፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
