
ደሴ፡ ኅዳር 28/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች የተመራ ልዑክ በደቡብ ወሎ ዞን በጊምባ ከተማ አሥተዳደር በወቅታዊ ክልላዊ እና ሀገራዊ የሰላምና የልማት ጉዳዮች ላይ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር እየመከረ ነው።
በውይይት መድረኩ ከደቡብ ወሎ ዞን ከመቅደላ፣ ከተንታ እና ከለጋምቦ ወረዳዎች እንዲሁም ከጊምባ እና ከአቀስታ ከተማ አሥተዳደር የተውጣጡ ልዩ ልዩ የኅብረተሠብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።
ወቅቱን የዋጀ እና ወሳኝ የውይይት መድረክ በመዘጋጀቱ ያመሰገኑት ተሳታፊዎች እንደ ሀገር ብሎም እንደ ክልል የሰላም እጦቱ እረፍት እንደነሳቸውና ዘላቂ ሰላም እንደሚሹ ተናግረዋል።
የተጀመሩ ሀገራዊ እና ክልላዊ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች እንዳይጠናቀቁ እና እንዳይሰፉ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ባንዳዎች አቅደው ይሠራሉ ብለዋል። ለክልሉ አለመረጋጋት ፈተና መደቀናቸውን ነው ያመላከቱት።
የአማራን ሕዝብ ነፃ እናወጣለን በሚል የተሳሳተ መንገድ ጫካ የገቡ ታጣቂዎች የአርሶ አደሮችን ሕይወት አክብደውበታልም ብለዋል።
የተኩስ ድምፅ ሰልችቶናል፤ ተረጋግቶ መኖር ናፍቆናል፤ ሰላም እንደሰማይ ርቆናል፤ ታግተን በነፍሳችን ማስያዣነት ገንዘብ መጠየቅ ይብቃን ብለዋል። ተሳታፊዎች በታሪካችን ሰምተናቸው የማናውቃቸው ዘግናኝ ጥፋቶች ሲፈፀሙ እየሰማን እያየን ነው ብለዋል።
የክልሉ ብሎም የወረዳዎች ሰላም የሚረጋገጠው ሁላችንም የሰላም ዘብ ስንኾን ነው ያሉት አስተያየት ሰጭዎች ከዚህ በላይ የተራዘመ የስቃይ እና የስቆቃ ጊዜ ማሳለፍ የለብንም ነው ያሉት።
በጫካ የሚገኙ አካላት ከማኅበረሰቡ የተሰወሩ አይደሉም ያሉት የውይይቱ ተሳታፊዎች የታጠቁ ኀይሎችን መክሮ ወደ ማኅበረሰቡ ማስገባት ይገባል ነው ያሉት። ለዚህ ተግባር ደግሞ በመንግሥት በኩል ተጠናክሮ የቀጠለው የሰላም አማራጭ ፍሬ እያፈራ መኾኑን ተናግረዋል።
ማኅበረሰቡ ከሃይማኖት አባቶች እና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር በመኾን ከልብ የመነጨ የሰላም ማስፈን ሥራ ሊሠራ እንደሚገባም ነው የተመላከተው።
በተለይ መንግሥት ለሥራ እድል ልዩ ትኩረት በመስጠት የወጣቶችን ጥያቄ መመለስ እንደሚገባም ተጠይቋል። የመንገድ፣ የጤና ተቋማት እና የንፁህ መጠጥ ውኃ እና ሌሎች የልማት ጥያቄዎችም እየተነሱ ነው።
ዘጋቢ:- ጀማል ይማም
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
