ወጣቶች ከተቀጣሪነት ወጥተው ሥራ ፈጣሪነት ላይ ሊያተኩሩ ይገባል።

16
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 28/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሦሥተኛው ዙር “ብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ ፕሮጀክት” ማጠቃለያ መርሐ ግብር ተካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ የተገኙት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በክልሉ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች ውስጥ የሥራ ዕድል ፈጠራ ዋነኛው ጉዳይ መኾኑን ገልጸዋል።
በዚህ ዓመት በከተማ አሥተዳደሩ የሥራ እድል ለመፍጠር ከታቀደው ከ48 ሺህ በላይ ወጣቶች እስከ አሁን ከ15 ሺህ በላይ ለሚኾኑት የሥራ እድል ተፈጥሮላቸዋል ብለዋል።
የሥራ እድል ፈጠራው ሥራ ለማግኘት አቅም የሌላቸውን ወጣቶች ጭምር ተጠቃሚ ያደረገ መኾኑንም ጠቅሰዋል። ሠልጣኞች በፈለጉት የሥራ መስክ ሠልጥነው የሥራ እድል ተጠቃሚ ያደረጉ ሥራ ፈጣሪ ድርጅቶችን አመስግነዋል።
በቀጣይም ሥራ ፈላጊዎች በሚጠበቀው መንገድ ሠልጥነው እንዲወጡ ድርጅቶች እና ተቋማት ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ ጠይቀዋል።
ሠልጣኞችም ከተቀጣሪነት ባለፈ በራስ አቅም ሥራ ፈጣሪ መኾን ላይ እንዲያተኩሩ አሳስበዋል። ከተማ አሥተዳደሩም የሚጠበቅበትን ለማድረግ ዝግጁ ነው ብለዋል።
በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የሥራና ክህሎት መምሪያ ኀላፊ ዘመነ አሰፋ ከተማ አሥተዳደሩ በፌደራል ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር እና ሌሎች ድርጅቶች ድጋፍ ወጣቶችን በተለያዩ ዙሮች ለስድስት ወር ያህል እያሠለጠነ ይገኛል።
ባለፉት ሁለት ዙሮች ከሠለጠኑት ከ2 ሺህ 700 በላይ ወጣቶች ውስጥ ከ99 በመቶ በላይ የሚኾኑት በተለማመዱባቸው እና በተለያዩ ድርጅቶች እንዲሁም በራሳቸው የሥራ አማራጭ የሥራ እድል እንደተፈጠረላቸው በማሳያነት አንስተዋል።
በዚህ ዓመትም 1 ሺህ 700 የሚኾኑ ወጣቶች በተለያዩ ሙያዎች ሠልጥነው ወደ ሥራ መግባታቸውን ነው የገለጹት።
የባሕር ዳር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዋና ዲን ፈለቀ ውቤ ኮሌጁ በተለያየ ዙር ወጣቶችን የተግባቦት፣ የጊዜ አጠቃቀም፣ የሥራ አፈላለግ እና የዲጂታል ክህሎት፣ በሥራ ላይ እንዴት ውጤታማ መኾን እንደሚቻል የአቻ ለአቻ ውይይት ሥልጠና በመስጠት ወደ ኢንዱስትሪዎች የተግባር ልምምድ እንዲያደርጉ እየሠራ ይገኛል ብለዋል። ሥልጠናው የወጣቶችን የሥራ ባሕል ለማጎልበት የሚያግዝ መኾኑን ነው የገለጹት።
የጁኒየር ጋርመንት እና ጨርቃጨርቅ ፋሽን ዲዛይን ድርጅት ባለቤት ሙሉጌታ ውለታው ድርጅቱ በሦሥት ዙሮች 139 ወጣቶችን አሠልጥኖ የሥራ እድል መፍጠሩን ገልጸዋል።
ከዚህ በፊት በድርጅቱ ተቀጥረው ይሠሩ የነበሩ ወጣቶች አሁን ላይ የራሳቸውን ድርጅት በማቋቋም ለሌሎች ወጣቶች ጭምር የሥራ እድል የፈጠሩ እንዳሉም ገልጸዋል። በቀጣይም ወጣቶችን የማሠልጠን እና የሥራ እድል ለመፍጠር ማቀዳቸውን አንስተዋል።
ትልልቅ ኢንዱስትሪዎችም ባላቸው አቅም ልክ ወጣቶችን በማሠልጠን የሥራ እድል መፍጠር ቢችሉ አሁን የሚታየውን የሥራ አጥነት ችግር መቅረፍ እንደሚቻል አንስተዋል።
የሽመና ሥልጠና ወስዳ የሥራ እድል የተፈጠረላት ወጣት መልሽ ሀብቴ ደግሞ ሥልጠናው አቅምን የሚያጎለበት፣ በራስ አቅም የራስን ዘላቂ ሥራ መሥራት የሚያስችል መሆኑን አንስታለች።
ዘርፉ ሰፊ የሰው ኀይል መያዝ የሚች መኾኑን የገለጸችው ሠልጣኟ በቀጣይ በራሷ ለመሥራት ፍላጎት እንዳላት አንስታለች።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleሙስና ሊታለፍ የማይገባው ቀይ መስመር ነው።
Next articleየአማራ ዴሞክራሲያዊ ኀይል ንቅናቄ (አዴኀን) 3ኛውን ድርጅታዊ መደበኛ ጉባኤ ጀምፘል።