ሙስና ሊታለፍ የማይገባው ቀይ መስመር ነው።

11
ባሕር ዳር: ኅዳር 28/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ “ትውልድን በሥነ ምግባር፤ ተቋምን በአሠራር መገንባት” በሚል መሪ መልዕክት የጸረ ሙስና ቀን ምክንያት በማድረግ ከቢሮው ሠራተኞች እና ከአቃብያን ሕግ ባለሙያዎች ጋር ምክክር አድርጓል።
የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኀላፊ ብርሃኑ ጎሽም
ሙስና የሕዝብ እና መንግሥትን ጥቅም የሚጎዳ የብልሹ አሠራር ዋነኛ መገለጫ ነው ብለዋል። በማኅበረሰብ ውስጥ የሞራል እና የሥነ ምግባር ውድቀትን በማምጣት ለማኅበራዊ ቀውስ ይዳርጋል ነው ያሉት።
የሕዝብ እና የመንግሥትን ሃብት እንደሚያወድም ነው የተናገሩት። ውስብስብ እየኾነ የመጣውን የሙስና ወንጀል ለመታገል ከተለመደው መንገድ በመውጣት መሥራት እንደሚገባም ገልጸዋል።
ሙስናን ለመከላከል ቁርጠኛ፣ ንጹሕ እና ብቁ መኾንን ይጠይቃል ያሉት ቢሮ ኀላፊው ከምርመራ ጀምሮ እስከ ፍርድ ሂደት ድረስ በአግባቡ መምራት ያስፈልጋል ብለዋል።
“ሙስና ሊታለፍ የማይገባው ቀይ መስመር ነው” ሲሉም ገልጸዋል። የችግሩን ጥልቀት እና አስከፊነት በመገንዘብ ሙስናን እና ብልሹ አሠራርን የማይሸከም ትውልድ መገንባት ላይ መረባረብ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በክልሉ ፍትሕ ቢሮ የጸረ ሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት የክትትል ዓቃቢ ሕግ ፈቃዴ ምሥጋናው ሙስና የማኅበረሰብን እሴት እየሸረሸረ የትውልድ ውድቀት እያስከተለ ስለመኾኑ አብራርተዋል። በተለይም በአገልግሎት ሰጭ ተቋማት ላይ አሳሳቢ እና ፈታኝ እየኾነ መምጣቱን አንስተዋል።
ቢሮው ትውልድ ላይ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ መሥራት፣ ቀድሞ የመከላከል እና ሕግ የማስከበር ሥራዎችን እያከናወነ ስለመኾኑ ነው ያነሱት። ለአብነትም በቅድመ መከላከል ሥራ ባለፈው ዓመት 16 ቢሊዮን የሚገመት ሃብት ማዳን እንደተቻለ አንስተዋል።
ያለ አግባብ ሊመዘበር የነበረን ከ132 ሚሊዮን ብር በላይ የሕዝብ ሃብት ማዳን እንደተቻለም ጠቅሰዋል። 12 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ወደ መንግሥት ማስመለስ እንደተቻለም ገልጸዋል።
አስተማሪ ቅጣት በማስቀጣት በኩል ባለፈው ዓመት በሙስና ወንጀል የ25 ዓመት ጽኑ እሥራት ማስቀጣት መቻሉንም ጠቁመዋል።
የውይይቱ ተሳታፊ ዐቃቢ ሕግ ጌታሰው ባንቲደር ሙስናን መከላከል የሁሉም ድርሻ መኾን እንዳለበት ተናግረዋል። የሙስና ወንጀል ውስብስብ በኾነ መንገድ የሚፈጸም በመኾኑ ተቋማትም ተቀናጅተው የቅድመ መከላከል ሥራ ላይ መሥራት እንደሚገባ አንስተዋል።
ማኅበረሰቡ የአመለካከት ለውጥ እንዲያመጣ የተቀናጀ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ መሥራት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
ዘጋቢ: አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበአዲስ አበባ ከተማ አራዳ ክፍለ ከተማ ሕዝባዊ ውይይት ተካሄደ።
Next articleወጣቶች ከተቀጣሪነት ወጥተው ሥራ ፈጣሪነት ላይ ሊያተኩሩ ይገባል።