
ባሕር ዳር: ኅዳር 28/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በምሥራቅ ጎጃም ዞን ከደብረ ወርቅ ከተማ አሥተዳደር እና ከእናርጅ እናውጋ ወረዳ ነዋሪዎች ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ እየተወያዩ ነው።
በውይይቱ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አሥተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር)፣ የምሥራቅ ጎጃም ዞን አሥተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሃኑ፣ በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ዕዝ አዛዥ ሜጄር ጄኔራል ብርሃኑ ጥላሁን እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን አሥተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሃኑ ደብረ ወርቅ እና አካባቢው የጥንታዊ አድባራት እና ገዳማት መገኛ መኾኑን ተናግረዋል። የአንድነት፣ የመተሳሰብ እና የፍቅር እሴት ባለቤት ነውም ብለዋል።
ይህ የቆዬ እሴት እና ባሕል ያለው ማኅበረሰብ ባለፉት ሁለት ዓመታት ዘርፈ ብዙ ጉዳት እንደደረሰበት ተናግረዋል። ማኅበራዊ ግንኙነት እንዳይኖር፣ አርሶ አደሮች እንዳያለሙ፣ ነጋዴዎች እንዳይነግዱ፣ ተማሪዎች እንዳይማሩ ኾኖ ቆይቷል ነው ያሉት። በማኅበረሰቡ ዘንድ ሥነ ልቦናዊ እና ማኅበራዊ ጉዳት እንደደረሰም በዕለቱ አንስተዋል። የተጀመሩ የልማት ሥራዎች በተያዘላቸው መንገድ እንዳይከወኑ እና ለወጣቶች የሥራ ዕድል እንዳይፈጠር አድርጎ ቆይቷል ነው ያሉት።
ከባሕል እና ከእሴት ያፈነገጠ አስነዋሪ ተግባር መፈጸሙንም ገልጸዋል። የውጭ ጠላቶች ተላላኪው ቡድን በደል ቢያደርስም በሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ በክልሉ የጸጥታ ኃይል እና በሰላም ወዳዱ ሕዝብ ምኞቱ ከሽፏል፤ በየአካባቢውም አንጻራዊ ሰላም ተፈጥሯል ነው ያሉት። የልማት ሥራዎችም እየተሠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል።
በርካቶች የሰላም አማራጭን እየተቀበሉ መኾናቸውን ገልጸዋል። ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ መወያየት እንደሚገባ ነው የተናገሩት። ለእውነት መቆም፣ ሰላምን መጠበቅ እና ለሰላም ጸር የኾነውን ታጣቂ ቡድን መታገል ይገባል ነው ያሉት።
ሰላምን በማረጋገጥ ጉዳት የደረሰበትን የትምህርት ዘርፍ መታደግ እና ትውልድን ማነጽ እንደሚገባም አመላክተዋል። በትብብር እና በአንድነት ሰላማችን እንመልሳለን ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) “ዘላቂ ሰላም ያለ ጠንካራ የባሕል እሴት ግንባታ ሊረጋገጥ አይችልም” ብለዋል። ሰላምን ለማጽናት የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው ተናግረዋል። የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ታላላቅ ችግሮችን የሚፈቱ እና ዘላቂ ሰላምን የሚያረጋግጡ ናቸው ብለዋል።
የአማራ ክልል ሕዝብ ባለፉት ዓመታት በችግር ውስጥ መቆየቱን ተናግረዋል። ችግሮችን በውይይት የመፍታት እና የመመካከር የቆየ እሴትም ችግር ገጥሞት እንደነበር ነው የገለጹት። ሰማይ ቢቀደድ ሽማግሌ ይሰፋዋል በሚባልበት ማኅበረሰብ ውስጥ ለእርቀ ሰላም የሄዱ ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች መዋረዳቸውን፣ መገረፋቸውን እና መገደላቸውን አንስተዋል።
ባለፉት ዓመታት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ መራቃቸውን የተናገሩት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ይህ ማለት ነገ ሕዝብ የሚመራ መሪ፣ የሚያክም ሐኪም፣ የሚያስተምር መምህር፣ መፍትሔ የሚያመላክት ምሁር አይኖርም ማለት ነው ብለዋል። ይህ ደግሞ ሕዝብን በእጀጉ የሚጎዳ እና ወደ ኋላ እንደሚያስቀር ተናግረዋል።
አሁን ያለው ችግር እንዲቋጭ መወያየት፣ መመካከር እና የጋራ መፍትሔ ማስቀመጥ ይገባል ነው ያሉት። ይህ ችግር ከዚህ በኋላ መቀጠል እንደሌለበትም ተናግረዋል። በመምከር ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን እንዲቀበሉ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።
አካባቢያቸውን እንዲጠብቁ እና ሰላማቸውን እንዲያረጋግጡም አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
