
ጎንደር: ኅዳር 28/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በጎንደር ከተማ እና አካባቢው ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ አካላት የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ገብተዋል።የሰላምን ጥሪ ከተቀበሉ አካላት መካከል በአማራ ፋኖ የጎንደሬ በጋሻው ክፍለ ጦር አመራር የነበረው አብነት አለምነህ እና በዳግማዊ ቴዎድሮስ አምስተኛ ኮር የኮር አመራር የነበረው ባብል ብርቁን ጨምሮ ሌሎችም ይገኙበታል።
የሰላም ጥሪውን የተቀበሉ አካላት የቡድን እና የነፍስ ወከፍ መሣሪያ ለመንግሥት ገቢ አድርገዋል። የተሳሳተ መንገድ መርጠው ትግል መጀመራቸውን የተናገሩት ታጣቂዎቹ በትጥቅ ትግሉ በርካታ የሀገር ሃብት መውደሙን ገልጸዋል።
የሰላም ጥሪውን የተቀበሉ አካላት የትጥቅ ትግሉ ሕጻናት ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዲኾኑ፣ እናቶች እና ሴቶች ለበርካታ ችግሮች እንዲጋለጡ ማድረጉንም ነው የተናገሩት። ከዚህ ቀደም በሕዝቡ ላይ የደረሱ በደሎች ዳግም እንዳይከሰቱ የሰላምን አማራጭ ተከትለው መግባታቸውንም አንስተዋል።
አሁንም በተለያዩ አካባቢዎች ነፍጥ አንግበው የሚታገሉ አካላት ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት የአማራን ሕዝብ ጥያቄዎች በሰላማዊ መንገድ እንዲመለሱ የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ከሰሞኑ በመንግሥት እና በአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት መካከል የተደረገውን የሰላም ስምምነት እንደሚደግፉም ገልጸዋል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ አለልኝ ዓለም በተለያዩ አካባቢዎች የታጠቁ አካላት መንግሥት ያቀረበውን የሰላም አማራጭ ተቀብለው ወደ ሰላማዊ ኑሮ እየተመለሱ መኾኑን አስታውቀዋል።
መንግሥት ሰላምን የመረጡ አካላትን በዘላቂነት ለማቋቋም እንደሚሠራም አንስተዋል።
የማኅበረሰቡን የዕለት ከዕለት ኑሮ የፈተነውን የትጥቅ ትግል በማቆም ችግሮችን በውይይት እና በድርድር ለመፍታት የሚያስችለውን የሰላምን አማራጭ መከተል እንደሚገባም ኀላፊው መልዕክት አስተላልፈዋል።
በቅርቡም በጎንደር እና አካባቢው ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች የቀረበላቸውን የሰላም ጥሪ መቀበላቸው ይታወሳል።
ዘጋቢ:- ቃልኪዳን ኃይሌ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
