
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 15/2012 ዓ.ም (አብመድ) በሰኔ 15/2011ዓ.ም የተሰው የአማራ ክልል መሪዎችና የፀጥታ ኃይል አባላት የታሰቡበት የፓናል ውይይት በባሕር ዳር ተካሂዷል፡፡
የፓናል ውይይቱ ሰማዕታቱ የሀገሪቷን የለውጥ ጉዞ መምራት የሚችል ተስፋ የተጣለባቸው እንደነበሩ በውይይቱ ቀርቧል፡፡
ሀገሪቷን ከመበተን አደጋ ታድገዋል፤ በምሁራን ላይ ያላቸው ዕምነት ከፍተኛ በመሆኑ ክልሉን በዕውቀት ለማሻገር ምሁራንን ወደፊት በማምጣት የሠሩ ናቸው፡፡ የክልሉን ልማት ለማፋጠን፣ ከለውጥ ባሕሪ ጋር ተያይዞ የመጣው የፀጥታ እና ቶሎ የመልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ ጥረት እያደረጉ ሳሉ የተሰው ሰማዕታት መሆናቸው በፓናል ውይይቱ ቀርቧል፡፡
የችግሩ ምክንያት ያለመናበብ፣ ያለመደማመጥ እና በጭብጨባዎች የተሳከሩ አካሄዶች በመስተዋላቸው መሆኑም ቀርቧል፡፡ ጥቂት ኃይሎች በቡድንና በጎጥ ጥቅም መተሳሰር፣ እንደሀገር የተሳከረው ፖለቲካ የክልሉ የሥራ ኃላፊዎችን ዋጋ እንዲከፍሉ አስገድዷል፡፡ ከለውጡ ማግሥት ሁሉም የየራሱን ሐሳብ ይዞ ተቆርቋሪ መስሎ መቅረብና በለውጡ በአጭር ጊዜ ሁሉም ጥያቄዎች እንዲፈቱ የማጯጯህ ችግሮች እንደነበሩም በውይይቱ ተነስቷል፡፡
ሕዝቡ በእርጋታው እና በአስተዋይነቱ ቆሞ አለመረጋጋቱ በሰላም እንዲፈታ የተጫወተውን ሚና በመጠቀም ከድርጊቱ ማግስት ከሁነቱ በመማርና በአንድነት ለአማራ ሕዝብ ከፍታ መሥራት እንደሚያስፈልግ በመፍትሔነት ተመላክቷል፡፡
በጥልቅ ሥነ ምግባር የሚመራ ሀቀኛ የመንግሥት ሥርዓት መፍጠር እንደሚገባም ተጠቁሟል፡፡ ጎጠኝነት የሌቦች የመታገያ የቃል ኪዳን ማዕከል እንዳይሆን መከፋፈልን በአንድነት መለወጥ እንደሚገባና ሀገራዊ ተሳትፎን ለማሳደግ የሚቀሩ ተግባራት በአግባቡ መምራት እንደሚያስፈልግም በፓናል ውይይቱ ተመላክቷል፡፡
ምሁራንም ‘‘ስታዲዬም ውስጥ ቁጭ ብለው ግብ ከመፈለግ ገብቶ በመጫወት ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል’’ ተብለዋል፡፡
የአማራ የፖለቲካ ኃይሎች የጋራ መታገያ የጋራ ግብ መፍጠር እንደሚገባም በውይይቱ ተነስቷል፡፡
በፓናል ውይይቱ ጎን ለጎን የደም ልገሳ መርሐ ግብርም ተከናውኗል፡፡
ዘጋቢ፡- ግርማ ተጫነ
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡
