አራት ዐይናው ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ

10
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 28/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ በሰሜን ሸዋ በመርሐ ቤቴ አውራጃ በታች ቤት ወረዳ ረመሸት ቀበሌ ደን አቦ ገዳም በተባለ ሥፍራ በ1871 ዓ.ም ነው የተወለዱት።
ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ 21 መጻሕፍትን የደረሱ ሲኾን «የኢትዮጵያ ታሪክ፡ ከንግሥተ ሳባ እስከ ታላቁ የዓድዋ ድል» የተሰኘውን የመጨረሻውን መጽሐፋቸውን በዚህ ሳምንት ኅዳር 23/1919 ዓ.ም ነበር አሳትመው ለንባብ ያበቁት።
ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ ሀገራቸውን በተለያየ ቦታ ከውጭ ጉዳይ እስከ ንጉሱ ዋና ተጠሪ ኾነው ያገለገሉ ለሀገራቸው ቀናኢ ሰው እንደነበሩም ይነገርላቸዋል።
ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ በዲፕሎማትነት ጃፓንን ጨምሮ በተለያዩ ሀገሮች የኢትዮጵያ ወኪል ኾነው ሠርተዋል። ከዚህም ሌላ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኾነውም አገልግለዋል።
ብላቴን ጌታ ኅሩይ በተደጋጋሚ እንደ እንግሊዝ፣ አሜሪካ፣ ግብጽ፣ ጣሊያን እና ፈረንሳይን ብሎም ጃፓንን የመሰሉ የውጭ ሀገራትን መጎብኘታቸውን፤ የሀገራቱንም የሥልጣኔ ደረጃ እና የተጠቀሟቸውን አጋጣሚዎች ከሀገራቸው በሥልጣኔ ወደ ኋላ መቅረት ጋር ባነጻጸሩ ቁጥር የሚሰማቸውን ቁጭት ባገኙት አጋጣሚ ይገልጹ እንደነበር የታሪክ ምሁሩ ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ ሀሳባቸውን በገለጹበት ጽሑፍ ላይ ሰፍሯል።
👉 የድንቅነሽ ግኝት
ከዛሬ 51 ዓመት በፊት በአፋር ክልል ውስጥ ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዓመታት በፊት የኖረችውን የሉሲ ድንቅነሽ አጽሟ የተገኘው 1967 ዓ.ም ነበር። በአፋር የአዋሽ ስምጥ ሸለቆ ውስጥ በዶናልድ ጆንሰን የሚመሩት የሳይንስ ሊቃውንት ናቸው ቅሪተ አካሉን ያገኙት።
በዚሁ ዓመት በዚህ ሳምንት ኅዳር 22/1967 ዓ.ም ታዲያ ተመራማሪዎቹ በቁፋሮ ያወጧቸው ከነበሩ ቁርጥራጭ ቅሪተ አካሎች እና የመገልገያ መሣሪያዎች በተለየ ሁኔታ በብዛትም በመጠኑም ከፍ ያለ እና ለምርምራቸው ፍንጭ የሚሰጥ ቅሬተ አካል በቁፋሮ አግኝተዋል።
በበረሃማው የአፋር ዝቅተኛ ቦታ ሐዳር ላይ በጣሉት ድንኳን ውስጥ ሊቃውንቱ ይህ ግኝት የፈጠረባቸውን ደስታ ያከበሩት ግን እንዲሁ አልነበረም። በዚያን ዘመን በገነኑት ዘቢትልስ በተባሉ ሙዚቀኞች የተቀነቀነውን “ሉሲ ኢን ዘስካይ ዊዝ ዘ ዲያመንድ” በሚለው ሙዚቃ አጅበው ነበር። እናም ይህ ሚሊዮን ዓመታትን የተሻገረ ቅሪተ አካል ስያሜ ከዚህ ሙዚቃ ጋር ተቆራኘ። ኢትዮጵያዊ ስያሜዋ ግን ድንቅነሽ ኾነ።
ሉሲ ወይም በኢትዮጵያዊ ስሟ ድንቅነሽ 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዓመታትን ተሻግራ የኖረች በመካከለኛ ዕድሜ ያለች ሴት መኾኗንም ተመራማሪዎቹ ለዓለም ይፋ አደረጉ። ከዚህ ባሻገር ቅድመ አያቶቻችን ቢያንስ ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዓመታት በፊት በሁለት እግራቸው መራመድ ይችሉ እንደነበር ለመጀመሪያ ጊዜ የተረጋገጠው በሉሲ አስደናቂ ግኝት ነው።
የሉሲ ቅሬተ አካል የዚያን ዘመን ሰው ይራመድ እንደነበር አሳይቷል፡፡ በአሜሪካው ክሊቭላንድ የተፈጥሮ ታሪክ ሙዚየም ፓሊዮአንትሮፖሎጂስት በኾኑት ዶናልድ ጆንሰን የተገኘው የሉሲ ቅሬተ አካል አውስትራሎፒቲከስ ከሚባለው ቀደምት ዝርያ የሚመደብ ኾኖ ተገኝቷል።
ምንጭ፦ ዘቢግኒንግ ኦፍ ሂውማን ካይንድ የተሰኘ መጽሐፍ እና የኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም
👉የአካል ጉዳተኞች ቀን
የአካል ጉዳተኞች ቀን በዚህ ሳምንት ኅዳር 24/1985 ዓ.ም ነበር በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዲከበር የተወሰነው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አዋጅ በማውጣት በየዓመቱ እንዲከበርም አድርጓል።
ይህ አዋጅ እንዲወጣ ምክንያት የኾነው ደግሞ የአካል ጉዳተኞች ይደርስባቸው የነበረው መገለል ነው። የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ በዓለም አቀፍ ደረጃ በትኩረት እንዲታይ ለማድረግ እንዲቻልም ታሳቢ ተደርጎ እንዲከበር ነበር የተወሰነው።
ምንጭ፦ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ድረገጽ
በምሥጋናው ብርሃኔ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“ሰላም እንዳይመጣ የሚፈልገው በግጭት የሚጠቀም ብቻ ነው” አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር)
Next articleበሆሳዕና ከተማ የምክክር መርሐ ግብር እየተካሄደ ነው።