“ለሰላም በአንድነት ከተነሳችሁ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰላምን ማረጋገጥ ትችላላችሁ” አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)

12

ደብረማርቆስ: ኅዳር 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በምሥራቅ ጎጃም ዞን ከመርጡለ ማርያም ከተማ አሥተዳደር እና ከእነብሴ ሣር ምድር ወረዳ ነዋሪዎች ጋር ተወያይተዋል።

ውይይቱ “ዘካሪ፣ መካሪ የሀገር ሽማግሌ እና የሃይማኖት አባት ለዘላቂ ሰላም እና ልማት” በሚል መሪ መልዕክት ነው የተካሄደው።

የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳደር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) “ለሰላም አንድ እርምጃ ወደፊት የተራመዳችሁ መኾናችሁን አይቻለሁ ብለዋል። ሕዝብ እና መንግሥት እየተወያዩ መፍትሔ ሲያስቀምጡ ዘላቂ ሰላምን በአጭር ጊዜ ማረጋገጥ ይቻላል ነው ያሉት።

መንግሥት ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪዎችን አድርጓል፤ በተደረገው ጥረት ውጤት ተገኝቷል፤ ይህ የሰላም ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። እኔ ካልኩት ውጭ ሌላ ሃሳብ አያስፈልግም የሚል፤ ንጹሐንን የሚያሰቃይ፤ በጉልበት የሚያምንን ጽንፈኛ ግን ዝም ማለት አይገባም ነው ያሉት።

የጽንፈኛው ቡድን አሰላለፍ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር መኾኑንም ገልጸዋል። የጽንፈኛው ግብር መዝረፍ፣ መስረቅ እና ንጹሐንን ማንገላታት እንደኾነም ተናግረዋል።

ጽንፈኛ ቡድኑ የሃይማኖት አባቶችን መግደሉን እና ማዋረዱንም አንስተዋል። እንዲህ አይነት ድርጊት የሚፈጽመውን ቡድን ማውገዝ እና መታገል እንደሚገባም ተናግረዋል። ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ተደጋጋሚ ውይይቶችን እና ምክክር ማድረግ እንደሚገባም ገልጸዋል።

ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የሕዝብ ሚና ታላቅ መኾኑን ተናግረዋል። ችግሮችን በውይይት ለመፍታት መንግሥት ሁሉንም የሰላም አማራጮች ተጠቅሟል ነው ያሉት። በተደጋጋሚ የተደረገው የሰላም ጥሪ በሺዎች የሚቆጠሩ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን መቀበላቸውንም አንስተዋል።

የሰላም አማራጭን በማይቀበሉት ላይ የሕግ ማስከበር ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመላክተዋል። ጽንፈኛ ቡድኑ ወደ ግጭት የገባው የአማራ ሕዝብን ጥያቄዎች ለማስመለስ ሳይኾን የራሱን ጥቅም ለማስከበር እና የታሪካዊ ጠላቶችን ግብ ለማሳካት ነው ብለዋል።

የአካባቢው መሪዎች ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ እንዲሠሩ ያሳሰቡት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ራሳቸውን ማጥራት እና ሕዝብን በማስተሳሰር መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል። የሕዝብን ችግር ለይተው መፍታት እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።

የውስጥ ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚገባም ገልጸዋል። የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ለሰላም መምከር እና መፍትሔ ማስቀመጥ እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።

ሕዝብን በማደራጀት ሰላምን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ “ለሰላምም በጋራ ከሠራችሁ እና በአንድነት ከተነሳችሁ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰላምን ማረጋገጥ ትችላላችሁ ነው ያሉት።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleክልሉ ካጋጠመው የሰላም ችግር ለመውጣት ወጣቶች ኀላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል።
Next article“ሰላም እንዳይመጣ የሚፈልገው በግጭት የሚጠቀም ብቻ ነው” አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር)