
ደብረ ብርሃን: ኅዳር 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአፍሪካ ለ19ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ18ኛ ጊዜ”የዳበረ የወጣቶች ተሳትፎ ለዘላቂ ልማት” በሚል መሪ መልዕክት የ2018 ዓ.ም የአፍሪካ ወጣቶች ቀን ክልላዊ ማጠቃለያ መርሐ ግብር በደብረ ብርሃን ከተማ ተከብሯል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የታደሙት በአማራ ክልል በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) ክልሉ ያጋጠመውን የሰላም ችግር ለመፍታት እና ከድህነት ለመላቀቅ በሚሠራው ሥራ ወጣቶች ታሪካዊ አሻራቸውን ማሳረፍ አለባቸው ብለዋል።
በሀገራዊ የልማት ሥራዎች ላይ ወጣቶች ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉም ዶክተር ድረስ ጠይቀዋል።
በቀጣይ የሚደረገው ሀገራዊ ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቅ ወጣቶች ያላሳለሰ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ዘላለም አረጋ 19ኛው የአፍሪካ የወጣቶች ቀን በክልል ደረጃ በተለያዩ ዝግጅቶች ሲከበር መቆየቱን ተናግረዋል።
በክልሉ ወደ ሥራ በተገባው የ25 ዓመት አሻጋሪ ዕቅድ የወጣቶችን ውሳኔ የመስጠት ክህሎት ለማሳደግ በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
የደብረብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ተሳትፏቸውን ለማሳደግ የሚያስችል ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
በወጣቶች አስተሳሰብ ግንባታ ላይ ቀጣይነት ያለው ሥራ መሥራት ይጠይቃልም ነው ያሉት።
በቀጣይም የከተማዋን ሰላም በማረጋገጥ ላይ ወጣቶች የያዙትን ንቁ ተሳትፎ አጠናክረው እንዲቀጥሉም አሳስበዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የአማራ ክልል፣ የሰሜን ሸዋ ዞን እና የደብረብርሃን ከተማ አሥተዳደር መሪዎች እና ወጣቶች ተሳትፈዋል።
ዘጋቢ፦ ወንዲፍራው ዘውዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
