
አዲስ አበባ: ኅዳር 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች የሚነሱ የመሠረተ ልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መኾኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናግረዋል።
”የጉባ ብስራቶች የመደመር መንግሥት ትሩፋቶች” በሚል መሪ መልዕክት በአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ሁሉም ክፍለ ከተሞች ሕዝባዊ ውይይቶች ተካሂደዋል።
ከአራዳ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች ጋር ውይይት ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በ2017 ዓ.ም ከተማ አሥተዳደሩ ከተለያዩ የማኅበረስብ ክፍሎች ጋር ውይይት ማድረጉን አስታውሰው በተካሄዱ ሕዝባዊ ውይይቶች የተነሱ የሕዝብ ጥያቄዎችን ለመፍታት ከተማ አሥተዳደሩ መሥራቱን አንስተዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ነዋሪዎችን የቤት ባለቤት ለማድረግ ብሎም በዝቅተኛ ክፍያ መከራየት እንዲችሉ የቤት አቅርቦትን ለማሳደግ እና ለማስፋት እየተሠራ መኾኑን አስረድተዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት 100 ሺህ ቤቶችን በመገንባት ቆጥበው ለሚጠባበቁ የመኖሪያ ቤት ፈላጊዋች የሚሰጥ ሲኾን 7ሺህ ቤቶችን በመገንባት ደግሞ ለአቅመ ደካሞች እንደሚተላለፍ ተናግረዋል።
ከተማ አሥተዳደሩ መሠረተ ልማትን ለማስፋፋት በጀት መድቦ እየሠራ ሚገኝ ሲኾን የመንገድ፣ የውኃ እና ሌሎች አቅርቦቶችን ለማስፋፋትም ሰፊ ዕቅድ መኖሩን አንስተዋል።
የአራዳ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎችም ከተማ አሥተዳደሩ የነዋሪዎችን ኑሮ ለማሻሻል የወሰደው እርምጃ የሚበረታታ መኾኑን አንስተዋል።
በኮሪደር ልማት ከተማው ውብ እና ጽዱ እንዲኾን ብሎም የዲፕሎማት ከተማነቷን የሚመጥን ልማት መካሄዱንም አንስተዋል።
የአረንጓዴ ልማቱ ወንዞችን ጽዱ ማድረጉን ጠቁመዋል። በወንዝ ዳርቻ ልማቱም የሚደነቅ ተግባር መከናወኑን ተናግረዋል።
ከተማ አሥተዳደሩ ካከናወናቸው ተግባራት ጎን ለጎን የሕዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራትን በማሳደግ የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችንም መፍታት እንደሚገባ አንስተዋል።
ዘጋቢ፦ ተመስገን ዳረጎት
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
