አመልድ በክልሉ የተራቆቱ አካባቢዎች ላይ ከስድስት ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታወቀ፡፡

451

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 16/2012 ዓ.ም (አብመድ) በባለፈው ዓመት የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር የተተከሉ ችግኞች የመጽደቅ ምጣኔ 70 በመቶ መሆኑን አመልድ አስታውቋል፡፡

የአማራ መልሶ መቋቋም እና ልማት ድርጅት (አመልድ) በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ የተራቆቱ መሬቶች ላይ 6 ነጥብ 8 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል የቅድመ ዝግጅት ሥራዎቹን ማጠናቀቁን አስታውቋል፡፡ በአመልድ የአካባቢ እና ደን ልማት ፕሮጀክት ዳይሬክተር ሰሎሞን አየለ ለአብመድ እንደተናገሩት የአካባቢ መራቆት፣ ድርቅ እና የአፈር መሸርሸርን በመቀነስ፣ የአካባቢ ሥነ-ምኅዳርን ለመጠበቅ ጉልህ ሚና ያላቸው ዕፅዋቶች ይተከላሉ፡፡

አመልድ በ2012 ዓ.ም የክረምት የአረንጓዴ ልማት ፕሮጀክት፣ ፋውንዴሽን ግሪን ኢትዮጵያ ፕሮጀክት፣ በኤፍ.ኤል.አር ፕሮጀክት እና አራተኛው ልማታዊ የምግብ ዋስትና ፕሮግራም በሚተገበሩባቸው አራት ዞኖች የተራቆቱ ተፋሰሶች ላይ የችግኝ ተከላው ይከናወናል፡፡ በሰሜን ወሎ፣ በማዕከላዊ ጎንደር፣ በደቡብ ጎንደር ዞኖች እና ዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በሐምሌ መጀመሪያ የችግኝ ተከላ መርሀ ግብሩን ለመከወን ዝግጅቱ ማጠናቀቁን አቶ ሰሎሞን አስታውቀዋል፡፡

ክልሉ በ2012 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ሊተክላቸው ካሰበው 1 ነጥብ 75 ቢሊዮን ችግኞች መካከል 6 ነጥብ 8 ሚሊዮኑ የአመልድ ድርሻ መሆኑን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡ ችግኞቹ የሚተከሉባቸው አካባቢዎች ሥነ-ምኅዳር የተጎዳ እና የአፈር ለምነታቸውን መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡ አቶ ሰሎሞን እንደነገሩን ተከላው በፕሮጀክት የሚካሄድ በመሆኑ ድጋፍ እና ክትትል በማድረግ የጽድቀት መጠኑን የተሻለ ያደርገዋል፡፡

የሚተከሉት ችግኞች በወል መሬት፣ በእያንዳንዱ አርሶ አደር ጥምር ምርት ለደን ተብለው በተለዩ አካባቢዎች እና በተቋማት ይዞታ ላይ እንደሚሆንም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡ የሚተከሉት ችግኞችም ለጥምር ግብርና፣ ለአካባቢ ጥበቃ፣ ለግንባታ፣ ለመልሶ ማገገም እና ለምግብነት የሚውሉ ይሆናሉ ብለዋል፡፡

አመልድ ባለፈው ዓመት ባካሄደው የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር በሁለት ጊዜ ቆጠራ ተካሂዶ 70 በመቶ የችግኝ ጽድቀት ምጣኔ መመዝገቡንም አቶ ሰሎሞን አስታውቀዋል፡፡ የመጽደቅ ምጣኔው ካለፉት ዓመታት የተሻለ ቢሆንም የመሬቱ መጎዳት፣ ተባይ፣ ጥራት የሌለው ችግኝ እና ልቅ ግጦሽ እንደችግር መታየታቸውን ጠቅሰዋል፡፡ የዘንድሮው የችግኝ ተከላ መርኀ ግብር በፕሮጀክት መያዙ እና ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር ስምምነት ላይ መደረሱ የተሻለ የጽድቀት መጠን ለማስመዝገብ መልካም አጋጣሚ መሆኑንም አቶ ሰሎሞን አንስተዋል፡፡

አመልድ ባለፉት 23 ዓመታት ከ131 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት ላይ 712 ሚሊዮን ገደማ ችግኞችን በመትከል ከክልሉ የደን ሽፋን ውስጥ 3 ነጥብ 6 በመቶ ድርሻ ማበርከቱን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡

በታዘብ አራጋው

ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡

Previous articleኢትዮጵያ በሕዳሴው ግድብ ድርድር ሰበብ የዓባይ ወንዝ ተጠቃሚነቷን የሚገድብ ስምምነት እንደማትቀበል አቶ ገዱ አንዳርጋቸው አረጋገጡ።
Next articleጎጠኝነት የሌቦች የመታገያ የቃል ኪዳን ማዕከል እንዳይሆን መከፋፈልን በአንድነት መለወጥ እንደሚገባ ተወያዮች አሳሰቡ፡፡