ሰላም ጠምቶናል፤ መገዳደል ይበቃናል።

6

ደብረ ማርቆስ: ኅዳር 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በምሥራቅ ጎጃም ዞን ከመርጡለ ማርያም ከተማ አሥተዳደር እና ከእነብሴ ሳር ምድር ወረዳ ነዋሪዎች ጋር ተወያይተዋል።

ውይይቱ “ዘካሪ፣ መካሪ የሀገር ሽማግሌ እና የሃይማኖት አባት ለዘላቂ ሰላም እና ልማት” በሚል መሪ መልዕክት ነው የተካሄደው።

የውይይቱ ተሳታፊዎች ጥሩ ባሕል፣ እሴት እና ሃይማኖት ያለን፣ ኢትዮጵያዊነት ያስተሳሰረን ነን ብለዋል። ኢትዮጵያ የውጭ ጠላቶች የሚፈልጓት፣ በቀጥታ ጦርነት ያልኾነላቸውን በእጅ አዙር ጦርነት ውስጥ እንድትቆይ የሚፈልጉ ጠላቶች ያሏት ሀገር ናት ነው ያሉት።

ችግሮችን ለመፍታት መፍትሔው እጃችን ላይ ነው፤ ግጭቶች የጠላት ማስፈፀሚያ መኾናቸውን በመገንዘብ ችግሮችን በውይይት መፍታት ይገባል ብለዋል። መሪዎች ሕዝብን አስተባብረው ለሰላም እና ለልማት መሥራት እንደሚገባቸውም አንስተዋል።

በአንድነት ከተነሳን፣ በፍቅር እና በመተባበር ከሠራን ሰላምን በአጭር ጊዜ ውስጥ ማረጋገጥ እንችላለን ነው ያሉት። ወደ ጫካ የወጡ ታጣቂዎችን ወደ ሰላም መመለስ እንደሚገባም ተናግረዋል።

የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ከልባቸው እንዲመክሩም ጠይቀዋል። ክልሉን ለችግር የሚዳርግ አካሄድን ማስቆም እንደሚገባም ተናግረዋል። ሀገርን የመጠበቅ ግዴታ አለብን፣ ከሀገር በላይ የሚበልጥ የለም፤ ሀገር የሁሉም ነገር መሠረት ነው፤ ሀገር እንዳናጣ አንድነታችንን እናጠናክር፣ ፍቅርን እናደርጅ፣ ችግሮቻችንን በውይይት እንፍታ ነው ያሉት።

በሰላም እየገቡ ያሉ ወንድሞች ተግባር የሚያስደስት ነው፤ ሌሎች እንዲገቡም መሥራት አለብን ብለዋል። ሰላም ጠምቶናል፤ መገዳደል ይበቃናል፤ ሰላምን እናውርድ ነው ያሉት። የውይይት አማራጮችን ማስፋት እንደሚጠቅምም ተናግረዋል።

ችግሩ ቀስ በቀስ ሁሉንም የሚበላ ነው ያሉት ነዋሪዎቹ አንድነታችንን በማጠናከር ሰላማችንን መመለስ አለብን ነው ያሉት። ልጆቻችን ለዓመታት ከትምህርት ገበታ ርቀው ተወዳዳሪ እንዳይኾኑ ኾነዋል፤ ተስፋ የምናደርግባቸው ልጆቻችን ተስፋቸውን ተነጥቀዋል ነው ያሉት። ልጆቻችንን አትንኩብን፣ ተተኪ እንድናጣ አታደርጉንም ብለዋል።

ግጭት፣ አለመተማመን፣ መከፋፈል እና መገዳደል ማንንም አይጠቅምም ነው ያሉት። አባቶቻችን የኢትዮጵያን አንድነት አስጠብቀው እንዳቆዩን ሁሉ እኛም አንድነቷን ማስጠበቅ ይገባል፤ በየወንዙ መከፋፈል ሀገር እና ሕዝብ ጎድቷል፤ ለኢትዮጵያ ክብር እና ታሪክም አይመጥንም ነው ያሉት።

ለሰላም የሚነሳሳ ልቡና እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። ሁሉም ሰው አንዳንድ ሰው ለሰላም ማምጣት አለበት፤ በተደናገረ ሃሳብ መኖር ይበቃል ነው ያሉት። ንጹሐን እየታገቱ ገንዘብ አምጡ እየተባለ ነው፤ ያላቸው ከፍለው ይወጣሉ፤ የሌላቸው ግን በዛው ቀርተዋል፤ በየቀኑ ገንዘብ አምጡ እየተባልን እየተደበደብን ነው፤ እንዲህ እየኾን መኖር ይበቃል፤ መንግሥትን እናግዘዋለን ሕግ ያስከብርልን ብለዋል።

ለሰላም ጠንቅ የኾኑ የመልካም አሥተዳደር እና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባም ተናግረዋል። ለወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር እንደሚጠበቅም አመላክተዋል።

ግጭትን ገንዘብ ያደረጉ ኀይሎች ግጭቱ እንዳይቆም እንደሚፈልጉም ገልጸዋል። የሰላምን አማራጭ የሚቀበሉ ካሉ ይምጡ እምቢ ካሉ ግን መንግሥት የተጠናከረ እርምጃ መውሰድ አለበት ነው ያሉት። ሕዝብ በአንድነት ከተነሳ የሚያቅተው ነገር እንደሌለ እና በጫካ ያሉት መድረሻ እንደሚያጡም ተናግረዋል።

የምሥራቅ ጎጃም ዞን አሥተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሃኑ ባለፉት ዓመታት የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ሕዝብን ለከፍተኛ ችግር መዳረጉን ገልጸዋል። የእስካሁኑ ይበቃል፤ ግጭቱን በማሳጠር ለሕዝብ ሰላም መፍጠር ይገባል ነው ያሉት። ለሰላም በአንድነት እና በመተባበር እንዲነሱም አሳስበዋል።

መርጡለ ማርያም ታላላቅ አባቶች የሚኖሩባት፤ ማኅበረሰቡም የአባቶችን ምክር የሚሰማባት ናት፤ ይሄን መልካም እሴት ለዘላቂ ሰላም መጠቀም ይገባል ነው ያሉት። የተፈጠረውን አንጻራዊ ሰላም ዘላቂ ለማድረግ በትኩረት እንዲሠሩም ጠይቀዋል።

ሕዝብ ታላቅ መስታውት ነው ያሉት አሥተዳዳሪው በውስጡ ያለውን ያያል፤ ያሳያል፤ መፍትሔም ያመላክታል ብለዋል። አንድ በኾነ ኅብረተሰብ ውስጥ የሰላም ችግር እንደማይፈጠርም ተናግረዋል። ሕዝብን እያሰቃየ ያለውን ኀይል ተው ማለት እንደሚገባም አመላክተዋል።

መንግሥት የሀገር እና የሕዝብ ኀላፊነት አለበት ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው ሁሉም ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን እንዲቀበሉ ይፈልጋል ነው ያሉት። የሰላም አማራጭን የማይቀበሉትን ግን እርምጃ እንወስድባቸዋለን ብለዋል።

በማኅበረሰቡ ውስጥ ተሰግስገው የሕዝብን ሰላም የሚነሱትን ማጋለጥ እንደሚገባም አስገንዝበዋል። የአካባቢው መሪዎች የአገልግሎት አሠጣጥ እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን እንዲፈቱም አሳስበዋል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የዳበረ ታሪክ፣ ባሕል እና ሃይማኖት ካለው ሕዝብ ግጭትን በምክክር መፍታት ይጠበቃል” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)
Next articleየፖሊስ ሠራዊቱ ሕብረ-ብሔራዊ አስተሳሰብን በመላበስ ለሚያገለግለው ሕዝብ ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት ተገለጸ።